ቀጥታ፡

የመዲናዋ አስተዳደር የይዞታ ማረጋገጫ የጠየቁ 137 አብያተ ክርስቲያናት ጥያቄዎች ይመልሳል

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 16/2012 የአዲስ አበባ አስተዳደር የይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄ ላቀረቡ 137 አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አንደሚሰጥ አስታወቀ። ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያኗና ምዕመኗ ላይ የሚደርሰው አደጋና ጥቃት እንዲቆም እንደሚሰራም ገልጿል። የደመራ በዓል አከባበር ስነ-ስርዓት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው። የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ የመዲናዋን ከንቲባ በመወከል ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 'አንደበታችንን የገራች፣ የአገራችንን ቋንቋ ያስተማረች የሁላችንም እናት ናት' ብለዋል። 'የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስታዝን ኢትዮጵያ ታዝናለች' ያሉት ኃላፊው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያኗና ምዕመኖቿ ላይ የሚደርሰውን አደጋና ጥቃት ከተማ አስተዳደሩ እንደሚያወግዝና ጥቃቱም እንዲቆም ከቤተክርስቲያኗ ጎን ሆኖ እንደሚሰራ ገልጸዋል። "ይህን የምናደርገው ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ስነ-ምግባር ይዛ ስለምትኖርና አሁንም ታሪክ እየሰራች ስላለች፤ ሁሌም ክብር ሊሰጣት የሚገባ በመሆኑ ነው" ብለዋል። ከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ በአዲስ አበባ የይዞታ ማረጋገጫ ላልነበራቸው ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠቱን አስታውሰዋል። በቀጣይም የይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄ ላቀረቡ 137 አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንደሚሰጣቸው አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም