በትግራይ ክልል በመቀንጨርና መቀጨጭ ችግር የሚጠቁ ህፃናት ቁጥር ወደ 49 ከመቶ ከፍ ማለቱ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በመቀንጨርና መቀጨጭ ችግር የሚጠቁ ህፃናት ቁጥር ወደ 49 ከመቶ ከፍ ማለቱ ተገለፀ
ኢዜአ መስከረም 16/2012 በተመጣጠነ ምግብ እጦት ምክንያት በህጻናት ላይ የሚከሰተው የመቀንጨርና መቀጨጭ ችግር ለመቅረፍ በትግራይ ክልል በተበታተነ መልኩ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አላመጡም ተባለ፡፡ በክልሉ በመቀጨጭና የመቀንጨር ችግር የሚጠቁ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ በስርዓተ ምግብና የህጻናት ጤንነት ዙሪያ የሚሰሩ አካላት ተቀናጅተው መስራት የሚያስችላቸውን አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል የምክክር መድረክ በማይጨው ከተማ ተካሄዷል። የፕሮግራሙ አስተባባሪና የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ግርማይ ወልደሳሜኤል ለኢዜአ እንደተናገሩት በትግራይ ክልል በርካታ ድርጅቶች በምግብና ስርዓተ ምግብ ዙሪያ ይሰራሉ፡፡ ''እነዚህ ድርጅቶች ስራውን በተበታተነ መልኩ የሚያከናውኑ በመሆኑ የህጻናት መቀንጨር እና መቀጨጭ ችግር ለውጥ እንዳያመጣ አድርጎታል'' ብለዋል፡፡ እነዚህ አካላት በጋራ ሰርተው ውጤታማ የሚሆኑበትን ስርዓት ለመዘርጋት የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የምግብና ስረዓተ ምግብ ባለሙያ ወይዘሮ ፍጹም አባይ በበኩላቸው ከሶስት ዓመት በፊት 39 ነጥብ 3 በመቶ የነበረው የህጻናት መቀንጨር እና መቀጨጭ ችግር አሁን ላይ 49 ነጥብ 7 መድረሱን ተናግረዋል፡፡ መቀንጨርና መቀጨጭ ህጻናት በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ ሳያገኙ ሲቀሩ የወደፊት ህይወታቸው ላይ አደጋ የሚያስከትል በሽታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከግለሰብ አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተመሳሳይ ስራ ያላቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራና በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ዕቅድ መያዛቸው በምግብና ስርዓተ ምግብ ያለውን የግንዛቤ ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል፡፡ የራያ አዘቦ ወረዳ የስነምግብ ባለሙያ ወይዘሮ ካሕሳ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው በምግብና ስረዓተ ምግብ ዙሪያ ያለውን የህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች በቂ አይደሉም ብለዋል፡፡ አሁን የተጀመረው በጋራ እንስራ ፕሮግራም በአንድ ጊዜ በርካታ አርሶ አደሮችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አመች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ኦፍላ ወረዳ የሰቆጣ የቃል ኪዳን ስምምነት አስተባባሪ አቶ ሀፍቱ ጸጋይ እንደተናገሩት በወረዳው የህጻናት መቀንጨር እና መቀጨጭ ችግር ለመከላከል ከግብርና፣ ጤና፣ ውሃ ትምህርት ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይና ከሴቶች ጉዳይ በጋራ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የህጻናት መቀንጨር እና መቀጨጭ በስፋት ከሚከሰትባቸው ወረዳዎች መካከል ኦፍላ ወረዳ አንዷ መሆኗን ገልፀው በአሁኑ ጊዜ 47 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ በወረዳው ስለምግብና ስርዓተ ምግብ ተግባቦትን በህብረተሰቡ በማስረጽ ከ47 ወደ 30 በመቶ ለማውረድ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ሀፍቱ ተናግረዋል፡፡ በምግብና ስርዓተ ምግብ የሚሰሩ አካላት በጋራ ለመስራት ማቀዳቸው የተያዘው ዕቅድ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የህጻናት መቀንጨር እና መቀጨጭ ችግር እስከ 2022 ዓም ዜሮ ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ይታወቃል።