ቀጥታ፡

ወደ ግሸን ለሚመጡ ምእመናን ልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘጋጀ

መስከረም 16/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለግሸን ደብረ ከርቤ በዓል የሚመጡ ምዕምናን በልዩ ሁኔታ የማጓጓዝ አገልግሎት ለመስጠት መስማማቱን የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ። በአውሮኘላን ኮምበልቻ አየር ማረፊያ ለሚደርሱ ምእመናንና ቱሪስቶችም የወሎ ዩኒቨርሲቲ አውቶብሶችን በመመደብ ግሸን ደብረ ከርቤ ድረስ በነጻ ለማጓጓዝ ቃል ገብቷል ተብሏል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ እንደገለጹት በአምባሰል ወረዳ መስከረም 21 ለሚከበረው ግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ከአገር ዉስጥና ዉጭ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በምእመናኑ ላይ ሊደርስ የሚችለውን መጉላላት ለመቅረፍ ከክልሉ መንግስትና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ አገልግሎት እንዲሰጥ ተከታታይነት ያለው ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። እንደ አቶ ሱለይማን ገለጻ አየር መንገዱም ጥያቄዉን ተቀብሎ ድርጅቱን በማይጎዳ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ ምዕምናኑን ለብቻ ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት ቃል ገብቷል፡፡ ''በዚህ መሰረትም በአዲስ አበባ በኩል የሚመጡ እንግዶችን መስከረም 19 እና 20 በልዩ ሁኔታ ኮምቦልቻ አየር ማሪፊያ ድረስ ለማጓጓዝ አየር መንገዱ ፕሮግራም ይዟል'' ብለዋል፡፡ መመለሻ ደግሞ መስከረም 22 እና 23 እንዲሆን በመወሰኑ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአዲስ አበባ በኩል የሚመጡት ምዕመናን ይህን እድል እንዲጠቀሙ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከኮምቦልቻ ግሸን ደብረ ከርቤ ያለዉን ጉዞ ደግሞ የወሎ ዩንቨርሲቲ አዉቶብሶች እንዲያመላላሱ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ቃል ገብቶ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለበዓሉ አስፈላጊዉ ቅድመ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን የእምነቱ ተከታዮች ወደ ቦታው መግባት ጀምረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም