ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ይሳተፋል - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ይሳተፋል
መስከረም 16/2012 ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች እንደሚሳተፍ አስታውቋል። የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ሕዳር 2012 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ይጀመራል። የፋብሪካው የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መኮንን ሸጋው ለኢዜአ እንደገለጹት በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉት የቮሊቦል ስፖርት እንዲያድግና እንዲጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው። የፋብሪካው ቦርድ በወንዶችና በሴቶች ክለብ ተቋቁሞ በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ እንዲሳተፍ መወሰኑንና የተጫዋቾች ምልመላ መጠናቀቁንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን /ኢሰማኮ/ የስፖርት ውድድሮች ፋብሪካውን ወክለው ሲሳተፉ የነበሩ ተጫዋቾች በቡድኖቹ ውስጥ ተካተዋል። ለዘንድሮው ዓመት ውድድር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡንም አቶ መኮንን ገልጸዋል። 'እንደ መጀመሪያ ተሳትፏችን በዘንድሮው ውድድር ልምድ መቅሰም ቀዳሚ ዕቅዳችን ነው' ያሉት አቶ መኮንን የምናገኘው ልምድ በቀጣይ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ያስችለናል ሲሉ ተናግረዋል። የሴቶች ክለብ መቋቋሙ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተዳከመውን የሴቶች ቮሊቦል ለማጠናከር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። በቮሊቦል ብቁ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ፋብሪካው የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም ነው አቶ መኮንን የገለጹት። ፋብሪካው በኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን /ኢሰማኮ/ የስፖርት ውድድሮች ዳርት፣ ጠረጴዛ ቴኒስና እግር ኳስ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ፋብሪካው በሁለቱም ጾታዎች ክለብ አቋቁሙ ለመሳተፍ መወሰኑ ስፖርቱን ስለሚያጠናክር ሊበረታታ እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይም የተዳከመው የሴቶች ቮሊቦል እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ክለብ ማቋቋሙም ለሌሎች ድርጅቶችና ተቋማት ዓርአያ ያደርገዋል ነው ያሉት። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሁለቱም ጾታዎች በሚያካሄደው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር ለማሳደግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ድርድር እያደረገ መሆኑንና በእስካሁን ሂደትም ጥሩ ምላሽ እያገኘ መሆኑን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም ጾታዎች የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በማካሄድ ላይ ይገኛል።