የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በዶሃ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በዶሃ ይጀመራል
አዲስ አበባ መስከረም 16/2012 17ኛው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ ይጀመራል። በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው የመክፈቻ ቀን በሴቶች ማራቶን የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ210 አገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 972 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን 1 ሺህ 54 ወንድ 918 ሴት አትሌቶች ናቸው። እ.አ.አ በ2017 በለንደን በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ያመጡ 44 አትሌቶች ያለ ምንም ማጣሪያ በቀጥታ በሻምፒዮናው ላይ ተሳታፊ ናቸው። በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት አልማዝ አያና፤ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሙክታር እድሪስ በለንደን አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊ ማምጣታቸው የሚታወስ ሲሆን በዘንድሮው ሻምፒዮና ያለ ጣሪያ ከሚሳተፉት አትሌቶች መካከል ይገኙበታል። ይሁንና አልማዝ አያና በጉዳት ምክንያት እንደማትሳተፍ ታውቋል። የሻምፒዮናው የመክፈቻ ስነ ስርአት ከምሽቱ 4 ሰአት ከ15 ደቂቃ 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ከሊፋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይካሄዳል። ኢትዮጵያም በሁለቱም ጾታዎች 38 አትሌቶችን የምታሳትፍ ሲሆን ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉ ርቀቶች አትሌቶቹ የሚወዳደሩባቸው ናቸው። የኢትዮጵያ የመጀመሪያ የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ከትናንት በስቲያ ዶሃ የገባ ሲሆን ውድድሩ በሚካሄድበት ከሊፋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምዱን እያደረገ ይገኛል። ሁለተኛው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን ወደ ዶሃ ያቀና ሲሆን ዛሬ ወደ ኳታር ርዕሰ መዲና እንደሚገባም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ዛሬ ሲጀመር የመጀመሪያ ሜዳሊያ የሚያስገኘው የሴቶች ማራቶን የፍጻሜ ውድድር ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ በአትሌት ሮዛ ደረጀ፣ አትሌት ሩታ ኣጋና አትሌት ሹሬ ደምሴ ትወከላለች። በማራቶን ውድድሩ የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን ያገኙ ሲሆን ሜዳሊያዎቹም ከአፍሪካ አገራት አትሌቶች አይወጡም የሚሉ ግምቶች በአትሌቲክስ ባላሙያዎች እየተሰጡ እንደሆነ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል። በማራቶን ውድድሩ ላይ 69 አትሌቶች ይሳተፋሉ። ከሴቶች ማራቶን የፍጻሜ ውድድር በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮችም ዛሬ ይካሄዳሉ። ከምሽቱ 1 ሰአት ከ 45 ደቂቃ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች የማጣሪያ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን በምድብ 1 አትሌት ሰለሞን ባረጋና አትሌት ሙክታር እድሪስ፣ በምድብ ሁለት አትሌት ጥላሁን ሃይሌና አትሌት አባዲ ሀዲስ ይሳተፋሉ። በሁለቱም ምድብ ከአንድ እስከ አምስት የሚወጡ አትሌቶች እንዲሁም በሁለቱም ምድቦች ፈጣን ሰአት ያስመዘገቡ አምስት አትሌቶች ተመርጠው በአጠቃላይ 15 አትሌቶች ወደ ፍጻሜው ውድድር የሚያልፉ ይሆናል። ከቀኑ 11 ሰአት ከ 10 ደቂቃ በ800 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ ብቸኛዋ ኢትዮጵያን የምትወክለው አትሌት ድርቤ ወልተጂ በምድብ አራት ባለው ማጣሪያ ትሳተፋለች። በስድስት ምድቦች በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከእያንዳንዱ ምድብ ሶስት አትሌቶች እንዲሁም አራት ፈጣን ሰአት ያላቸው በድምሩ 22 አትሌቶች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፋሉ። ከምሽቱ 12 ሰአት ከ 55 ደቂቃ በሚካሄደው የ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች በምድብ አንድ አትሌት መቅደስ አበበ በምድብ ሁለት አትሌት ሎሚ ሙለታ በምድብ ሶስት አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ የሚሳተፉ ይሆናል። ከሶስቱም ምድብ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ አትሌቶች እንዲሁም ፈጣን ሰአት ያላቸው ስድስት በድምሩ 15 አትሌቶች ወደ ፍጻሜው ውድድር የሚያልፉ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ በአትሌቲክስና በሜዳ ተግባራት የተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮች በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን ይካሄዳሉ። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2017 በለንደን በተካሄደው 16ኛው የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለት የወርቅና በሶስት የብር በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። አሜሪካ፣ኬንያና ደቡብ አፍሪካ በለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አገራት ናቸው። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎ ታሪኳ 27 የወርቅ 25 የብር 25 የነሐስ በድምሩ 77 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። አሜሪካ፣ ኬንያና ታላቋ ብሪታኒያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ታሪክ ብዙ ሜዳሊያ በማግኘት ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። 17ኛው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።