በአዲስ አበባ ላይ በስፖርት ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይገባል---ኢንጅነር ታከለ ኡማ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ላይ በስፖርት ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይገባል---ኢንጅነር ታከለ ኡማ
መስከረም 16/2012 አዲስ አበባ ላይ በስፖርት ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይገባል ሲሉ ምክትል ከንቲባው ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናገሩ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል። በጉባኤው ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የስፖርት ምክር ቤቱ ሰብሳቢና የከተማው ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ባስተላለፉት መልዕክት ስፖርት ከተማውን ለማስተዋወቅ ትልቅ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል። ስለሆነም በስፖርቱ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ስፖርት የህዝቡን ጤና በማስጠበቅ፣ ከተማዋን በበጎ በማስተዋወቅ እና ወጣቶች ጊዜቸውን የሚያሳልፉበትና የሚዝናኑበት ዘርፍ በመሆኑ የከተማ አስተደዳሩ አንዱ የትኩርት መስክ መሆኑንም አመላክተዋል። የስፖርት ምክር ቤት አባላትም ስፖርቱ መሰረታዋ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያግዝ ሀሳብ በማመንጨት ዘርፉ የሚያድግበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባቸዋል ሲሉ ኢንጅነር ታከለ ተናግረዋል። በተለይም ባሳለፍነው ዓመት የተጀመረው የማስ ስፖርትን ህብረሰቡ ባህሉ አድረጎ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። የማስ ስፖርት ኅብረተሰቡ በህል እንዲያደርገውና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተማ አስተደዳሩ አስፈለጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም ነው የገለጹት። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው የምክር ቤቱ አባላት በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት በቶክዮ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድርን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን እንዲሠራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በጉባኤው ለይ የፌደራሉ መስሪያ ቤት ባለፈው ዓመት ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ወደ ስፖርት ኮሚሽን ቢቀየርም እስካሁን ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ቢሮ ስያሜ ላይ ማሻሻያ እንዳልተደረገ በጉባኤው ላይ ተነስቷል። ከዚህ በፊት የአዲስ አባበ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተብሎ ይጠራ የነበረውን አደረጃጀት ለሁለት በመክፈል የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ በሚል ስያሜ የሚጠሩ መስሪያ ቤቶች እንዲቋቋሙ በጉባኤው ላይ መወሰኑም ታውቋል። ጉባኤው ከዚህ በተጨማሪም የስፖርት ምክር ቤት የክፍያ ተመንና የስፖርተኞች የላብ መተኪያ ክፍያ ማሻሻያን አጽድቋል።