ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና ሱዳን የመጣው ለውጥ ለአገራቱ የኢኮኖሚ ውህደት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው

ጋምቤላ (ኢዜአ) መስከረም 15 /2012 በኢትዮጵያና ሱዳን የመጡ ለውጦችና ማሻሻያዎች በአገራቱ መካከል የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ። "ኢትዮ-ሱዳን ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ 5ኛው የኢትዮጵያና ሱዳን ቢዝነስ ምክር ቤት ፎረም  በአዲስ አበባ ተካሄዷል። በፎረሙ ላይ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያና በሱዳን እየተካሄዱ ያሉ ለውጦችና ማሻሻያዎችን አገራቱ በኢኮኖሚ ለመዋሃድ እያደረጉ ላሉት እንቅስቃሴ የሚያበረከትውን አስተዋጽኦና መጠቀም በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል። ኢትዮጵያና ሱዳን ለረጀም ጊዜ የቆየ የወንድማማችነት ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት አገራቱ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማሸጋገር እየሰሩ ይገኛሉ። የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገች እንደሆነና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያሉት ለውጦችንም የሁለቱም አገራት የቢዝነስ ማህበረሰቦች ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። ሱዳን በግብርናና አግሮ ኢንዱስትሪ እምቅ አቅም ያላት እንዲሁም የቢዝነስ ማህበረሰቧ ጠንካራና ከቀጠናው ጋር ጥሩ ትስስር ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ይሄንን እድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ተናግረዋል። ለታላቅ ቀጠናዊ ውህደት መሰረት ለመሆን  የኢትዮጵያና የሱዳን ህዝብ በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም በማውሳት። በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በበኩላቸው አገራቱን ለማገናኛት እየተገነቡ ያሉ መንገዶች፣ የሱዳን ወደብ እንዲሁም ሌሎች ስራዎች ለኢኮኖሚው ውህደቱ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል። የሱዳን ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት ማግኘት ላይ ያሉ ቢሮክራሲዎችና ቀረጥን እንደ ዋነኛ ችግሮች እንደሚያነሱና ለሚያነሷቸው ጉዳዮችም ምላሽ ለመስጠት ከባለሀብቶቹ ጋር ይመከራል ብለዋል። የኢትዮጵያና ሱዳን ቢዝነስ ምክር ቤት ፎረም ፕሬዚዳንት ሚስተር ማጂድ ሜርጋኒ በአገራቱ አሁን ያሉ ለውጦችን ከተቀጠምን ያለ ምንም ጥርጥር አገራቱን ወደ ሚፈለገው የኢኮኖሚ ውህደት ማምጣት ይቻላል ብለዋል። የአፕኮ የጉዞ እና የቱር ኤጀንሲ ባላቤት ሚስተር አዲል አህመድም  ላለፉት 29 ዓመታት በኢትዮጵያ በማስጎብኘት፣በሪል ስቴትና መኪና በማከራየት ሲሰሩ መቆየታቸውን ይገልጻሉ። የሱዳን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ አሁን ጥሩ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዳለና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚመክሯቸውም ተናግረዋል። በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የሱዳን ብሔራዊ የኢንቨስትመንት ተቋም በአገራቱ ስለሚገኙ የኢንቨስትመንት እድሎችና አማራጮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የአገራቱን የኢኮኖሚ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በኢትዮጵያና በሱዳን ባለሀብቶችና ተቋማት መካከል የአቻ የንግድ ለንግድ ውይይትም ተካሄዷል። በተጨማሪም የአገራቱ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ይገባልም ተብሏል። የሁለቱ አገራት የቢዝነስ ማህበረሰበችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በፎረሙ ላይ ተሳትፈዋል። የሁለቱ አገራትን የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳለጥና በአገራቱ መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ትግበራ እንዲቀየሩ የኢትዮጵያና ሱዳን ቢዝነስ ምክር ቤት እ.አ.አ በ2009 መቋቋሙ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ወደ ሱዳን በዋነኛነት ቡና፣ ሻይ፣ የስጋ ውጤቶች፣ ቅመማ ቅመም እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ስትልክ ነዳጅ፣ የማጥለያ/የማጣሪያ ምርቶች፣ የዘይት ምርቶች፣ ጥራጥሬ፣ የመድሐኒት ምርቶችና የሴራሚክ ውጤቶችን ደግሞ ታስገባለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም