ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ዘመኑ ሰላማዊነት አስፈላጊውን ዝግጅት ማደረጉን አስታወቀ

78
ጋምቤላ (ኢዜአ) መስከረም 15 / 2012 ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክትር ከተማ ጥላሁን ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የዓመቱን  የመማር ማስተማር ሥራ ስኬታማ ለማድረግ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ከአገልግሎት አቅርቦት ችግሮች ጋር በተያያዘ ከገጠሙት ችግሮች በስተቀር የተሻለ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማሳለፉንም አስታውሰዋል። ባለፈው ዓመት በተለይም ከንጹህ መጠጥ ውሃ እቅርቦት፣ ከመብራት አገልግሎትና ዩኒቨርሲቲው አጥር የለውም በሚል ተማሪዎች ቅሬታ ሲቀርቡ እንደነበረም አታውሰዋል። ዶክተር ከተማ እንዳሉት የኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት በተማሪዎች የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በቅድመ ዝግጅት ሥራው ትኩረት ስጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። በትምህርት ዘመኑ በሀገሪቱ የተቀረጸውን አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ በመተግበር ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ለማፍራት ዩኒቨርሲቲው ትኩረት መስጠቱንም አመልክተዋል። ለእዚህም ዘንድሮ በፍኖተ ካርታው መሰረት ለሚቀበላቸው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ለሚሰጡ ትምህርቶች ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የስልጠና የማኑዋል ማዘጋጀቱን አመልክተዋል። የኒቨርሲቲው የዕፅዋት ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር በሱፍቃድ እንደግ በበኩላቸው ዘንድሮ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የሚጀመርበት በመሆኑ ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ ዝግጅት ማድረጋቸውን  ተናግረዋል። የትምህርት ዘመኑ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደው ውጤታማ ለማደረግም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ኮሚቴ በማቋቅም እየሰሩ መሆናቸውን ረደት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል። ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ቱት ጆን በሰጠው አስተያየት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎች የመጡበትን የትምህርት ዓላማ እንዲያሳኩ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የበኩሉን እንደሚወጣ አመልክቷል። ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢ ለሚመጡ ተማሪዎች አቀባበልና የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ፋዲን ዛን የተባሉ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ናቸው። "የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው የትምህርት ዘመን አዲሶቹን ጨምሮ ከሦስት ሺህ 700 በላይ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን ታውቋል" ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም