ቀጥታ፡

የሒሳብ አያያዝና ኦዲት መርሃችን የወደፊቱን የዕድገት ደረጃችን ጠቋሚ ነው

መስከረም 15 ቀን 2012  (ኢዜአ)  የአገራችን ተቋማትና ድርጅቶች አለም በደረሰባቸውና ወጥነት ባላቸው የሒሳብ አያያዝ መርህ መመራት መጀመራቸው የወደፊት የዕድገት ጉዞዋ የት እንደሆነ አመላካች መሆኑን የሒሳብ ባለሙያዎች አመራሮች ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ባወጣቸው አዋጅና ደንብ ላይ ከሒሳብ ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር መክሯል። መድረኩ በዋናነት የሁሉም ተቋማት የሒሳብ ባለሙያዎች የህዝብን ጥቅም ባስጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት ስርዓትና ወጥነት ባለው አለም አቀፋዊ ስርዓቱን ተከትለው እንዲሰሩ ለመምከር የተዘጋጀ ነው። ተሳታፊዎቹ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ስርዓታችን ከተለምዷዊው ወጥተው የአለም አቀፍ የኦዲት ደረጃዎችን ባሟላ መልኩ እንዲከናወን እንዲሁም አዋጅና መመሪያውን የሚከታተል ቦርድ መቋቋሙን በመልካም ጅምርነቱ ነው ያዩት። ይህም ተቋማቱ የዕለት ተዕለት ስራቸውን ለሙያተኛው በመስጠት ከዘልማዳዊ ስርዓት እንዲወጡ ያስችላልም ብለዋል። እንዲሁም ተቋማት አንድን ነገር ተግባራዊ ሲያደርጉም በባለሙያዎቹ ከተሰራው የሒሳብ ሪፖርት ተቋማቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እንደ ማመላከቻ ይጠቀሙበታልም ተብሏል። በዚሁ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተሳታፊ ተቋማት ሒሳብ ባለሙያዎችና አመራሮችም ያነሱት ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባገኙት አሰራሮች መመራቷ ከተቋማዊ ፋይዳውም በላይ አገራዊው እንደሚበልጥ ነው የሚያብራሩት። ከሻንዳንግ የቻይና መንገድ ስራ ድርጅት የሒሳብ ባለሙያው አቶ ያሬድ ምትኩ ደግሞ ጅማሮው  ተቋማት መረጃቸውን ለሁሉም በወጥነት ሪፖርት እንዲያደርጉ ያስችላል ነው ያሉት። የቦርዱ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ደበሌ በበኩላቸው የተቋማት ሪፖርት ከዚህ በፊት ወጥነት ስለሌለው አገሪቷ በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም በስራ ዕድሉ ያጣችው እንዳለ አንስተዋል። እንደዚሁም የሙያ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ በሙያው ተሰማርተው በሚገኙ አካላት ላይ  ቦርዱ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ባለሙያዎች የተቋማቱን ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያው የህዝብን ጥቅም ባስጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት ስርዓትን ተከትሎ አዋጁ ከወጣበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ መቆየቱ ነው የተገለጸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም