የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት የሚያሟላ እንጂ የተፋሰሱን ሃገራት የሚጎዳ አይደለም...የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት የሚያሟላ እንጂ የተፋሰሱን ሃገራት የሚጎዳ አይደለም...የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር
ኢዜአ መስከረም 15/2012 ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ተፈጥሯዊ በሆነው መብቷ ተጠቅማ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ የተፋሰሱን ሃገራት ጥቅም ሳትጎዳ የምታከናውነው እንደሆነ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ። ሚኒስትሩ በግድቡ የግንባታ ፕሮጀክት ጉብኝት ላይ ለተሳተፉ የሃገር ውስጥ እና የውጪ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ሃገሪቱ አባይን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀምና ልማቷን ማፋጠን መብቷን መጠቀም ይጠበቅባታል። ይሄንን የመልማት ፍላጎቷንና መብቷን በመጠቀም ሒደት በተለይም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተያይዞ የታችኛውን የተፋሰሱ ሃገራት ላይ ጉዳት የማይደርስ መሆኑንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ሳሊኒን ጨምሮ በስድስት ተቋራጮች ሥራው የሚካሄደው የህዳሴው ግድብ ከዚህ ቀደሞ በሜቴክ የተፈጸሙ ስህተቶች ተስተካክለው አሁን ከ68 ነጥብ 3 በመቶ በላይ መድረሱንም ገልጸዋል። ግንባታው በመፋጠን ላይ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስህተት የነበረባቸው ሁለት የቅድሚያ ሃይል ማመንጫ የብረት ስራዎች ላይ ማረሚያ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሃገሪቱ በግድቡ የውሃ አሞላል ላይ ለዓመታት ከተፋሰሱ ሃገራት ጋር ውይይት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰው የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና የግብጽ ባለሙያዎች በጋራ የሚያደርጉትን ጥናት በአብነት አንስተዋል፡፡ "በእያንዳንዱ የግድቡ ጉዳይ ላይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ስንነጋገር ቆይተናል" ያሉት ሚኒስትሩ ሃገሪቱ ዛሬም በፕጀክቱ ላይ የያዘችው አዲስ አቋም እንደሌለ ተናግረዋል። የህዳሴው ግድብ መገንባት በርካታ አስተዋጽኦ በቀጠናው አሳድሯል የሚሉት ሚኒስትሩ አሉታዊ ተጽእኖዎች እንዳይኖሩ ከሃገራቱ ጋር እየተሠራ መሆኑንም አብራርዋል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1959 ኢትዮጵያ ያልፈረመችበትን የቅኝ ግዛት የዐባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት እንድትቀበል የማድረግ ጥረትም እንደማትቀበለው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ አስታውቀዋል፡፡ "በአጠቃላይ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን ሃብት እና ንብረት ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ግንባታውን በ2015 ለመጨረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። ህብረተሰቡም ሥራውን በስፍራው በመገኘት ጭምር በመጎብኝት የግንባታውን ተጨባጭ ሁኔታ በመከታል ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።