ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሰራተኞቹ ጋር ግንኙነት የሚፈጥርበት የሬድዬ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ አዋለ

አዲስ አበባ  መስከረም 15/2012 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሰራተኞቹ ጋር በሬድዬ ግንኙነት በመፍጠር አገልግሎቱን የሚያቀላጥፍበት 'የአስትሮ ሞቶሮላ የሬድዬ ኮሙኒኬሽን ፕሮጀክት' አስመረቀ። የፕሮጀክቱ ምረቃ ስነ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በተገኙበት በእንጦጦ ማሪያም የቴሌ ማይክሮዌቭ ማሰራጭያ ጣቢያ ተካሂዷል። በሁለት ምዕራፍ የተከፈለውን ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለማስገባት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ሐምሌ 15 /2017 በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና በሞቶሮላ ሶሉሽን ኩባንያ መካከል ስምምነት ተፈርሞ ነበር። የመጀመሪያው ምዕራፍ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ኦሮሚያ ዞን ላይ ተግባራዊ ሆኗል። የኤሌክትሪክ የአገልግሎት አሰራሩን በማቀላጠፍ ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት እንደሚሰጥ የታመነበት ይሄው ፕሮጀክት 6 ቡድኖችን በመያዝ በ 8 የግንኙነት ቻናሎች በጋራ እና በእኩል ሁኔታ እንዲጠቀሙ የሚያግዝ ነውም ተብሏል። የአስቸኳይ ጥገና ሥራን ማቀላጠፍ፣ ከሰብ ስቴሽን ጋር የሚኖረውን ግኝኑነት ማሳለጥ፣ በግንኙነት ክፍተት ሊፈጠሩ የሚችሉ የሰውና የንብረት አደጋን መቀነስ እንዲሁም የኃላፊዎችን መረጃ የመቀበልና መልዕክት የማስተላለፍ ሥራውን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተገልጿል። በኤሌክትሪክ አገልግሎት የአውቶሜሽንና ኢነርጂ ማኔጅመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደመቀ ሮቢ አገልግሎቱ ስራውን የሚያከናውነው በስልክ እንደነበር አስታውሰው ይህም የሚሰጠው አገልግሎት ቅልጥፍና እንዳይኖረው አድርጎት ቆይቷል ይላሉ። ዛሬ የተመረቀው 'የሬድዮ ኮሙኒኬሽን ፕሮጀክት' መስክ የወጡ የጥገና ሰራተኞች ቢሮ ካሉ ሰራተኞች ጋር በፍጥነት እንዲገናኙ ከማድረጉም ባለፈ ከፍተኛና ዝቅተኛ ኃይል መስመር ላይ ካሉ ኦፕሬተሮች ጋርም በቀላሉ በመገናኘት ፍጥነት ያለው የጥገና አገልግሎቶች እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል። በዚሁ የመጀመሪያው ምዕራፍም በአዲስ አበበና ፊንፊኔ ዙሪያ በእጅ የሚያዙ 300 እንዲሁም 200 መኪና ላይ የሚገጠሙና 100 በጥሪ ማዕከልና በአስቸኳይ ጥገና ማዕከላት ላይ የሚገጠሙ ዲጂታል ሬዲዮኖች ጥቅም ላይ ውለዋል። እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክቱንም ለማካሄድ ከአዲስ አበባ ውጪ 8 ከተሞች የተመረጡ ሲሆን ለዚህም ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት ተይዞለታል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም