ለመስቀል ክብረ በዓል ለሚታደሙ የውጭ አገራት ጎብኝዎች ቆይታቸው እንዲሰምር ዝግጅት ተደርጓል-ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለመስቀል ክብረ በዓል ለሚታደሙ የውጭ አገራት ጎብኝዎች ቆይታቸው እንዲሰምር ዝግጅት ተደርጓል-ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ መስከረም 15/2012 በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የደመራና መስቀል ክብረ በዓል ታዳሚ የውጭ እንግዶች የአገር ውስጥ ቆይታቸው እንዲሰምር ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የባህልና ቱሪዘም ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎቶ አሰሪዎች ፌደሬሽን በበኩሉ የውጭ አገር ቱሪስቶች በቆይታቸው ረክተው አንዲመለሱ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል። በዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ በማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት የተመዘገበው መስቀል መስከረም አጋማሽ ማለትም ነገ በሚደረገው የደመራ ክዋኔ ይጀምራል። በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ታሪኩ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት መስቀል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገር ካበረከተቻቸው የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑንም አውስተዋል። የመስቀል በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ማህበራዊ ገጽታው የሚጎላበት እንደሆነ ገልጸው፤ አገር በቀል ባህል፣ ወግ፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና የሚንጸባረቅበትና የመቻቻል ማህበራዊ እሴቶች የሚታይበት በዓል መሆኑንም ገልጸዋል። በተለይም የደመራ ክዋኔ ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓለነቱ ባሻገር ማኅበራዊ ፋይዳው የጎላበትና ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚታይበት በመሆኑ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉትን የባህልና ቱሪዝም አደረጃጀቶችን በመጠቀም በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በደማቁ ለማክበር ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል። የአደባባይ በዓላት ከጊዜ ወደ ጊዜ የውጭ አገር ቱሪስቶችን የመሳብ አቅማቸው እያደገ መምጣቱን አስታውሰው፤ ለአብነትም በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2009 የጎብኝዎች ቁጥር 137 ሺህ የነበረ ሲሆን በ2018 ወደ 400 ሺህ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል። በዘንድሮው የደመራ ክብረ በዓል የሚታደሙ የውጭ አገር እንግዶች የአገር ውስጥ ቆይታቸው የሰመረ፤ ደህንነታቸውም የተጠበቀ እንዲሆን ከቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ከጸጥታና ደህንነት ተቋማትና ከሆቴል አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ጋር በመሆን ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል። በተለይም ከሆቴል አገልግሎት ጋር ለመስቀልና መሰል ክብር በዓላት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ለሚመጡ ጎብኝዎች የተመቸ አገልግሎት እንዲፈጠርላቸው የሆቴል ደረጃ ምደባ ስራዎችን ጨምሮ የተለየዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን አንስተዋል። የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት አሰሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት የስመዘገበቻቸው ክብረ በዓላት ሆቴሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያለው የቱሪስት ፍሰት በብዛት ከኮንፈረንስ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የእንግዶችን ወጭ ሌላ አካል ሊሸፍንላቸው ስለሚችል በተለይም በአዲስ አበባ የሆቴል አገልግሎት ውድ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ አድርጓታል ነው ያሉት። በዚህም በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ አገር እንግዶች ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል በአገልግሎት መስኮች የዋጋ ማሻሻያ ስራዎች እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል። በዘንድሮው የደመራና መስቀል በዓል ለሚመጡ እንግዶችም የባህላዊ ምግብ አቅርቦትና የዋጋ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የፌደሬሽኑ አባል ሆቴሎች ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። ቱሪስቶች ለኢትዮጵያ አምባሳደሮች እንዲሆኑና በደመራ በዓል እንቅስቃሴ ስለሚኖር እንግዶችን ከደመራ ስፍራዎች ለማንቀሳቀስና አቅጣጫዎችን የመሳየት ትብብሮችም በሆቴል ሰራተኞች እንደሚደረግ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት በተለዬ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና መሰል የመስህብ ሃብቶች ቢኖራትም እጅግ ዝቅተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለባትና ከዘርፉ ተጠቃሚ ያልሆነች አገር መሆኗን አቶ ፍትህ ገልጸዋል። ለዚህም ዋናው ችግር የገጽታ ግንባታና እምቅ ሃብንቶችን የማስተዋወቅ ስራዎች አለመኖርና ከሰላምና ፀጥታ አኳያ የሚሰጠው መረጃም የተዛባ መሆኑ እንደሆነ አንስተዋል። ፌደሬሽኑ በዚህ ረገድ ከባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ የመስራት ስራዎች ከመጀመሩ በተጨማሪ፣ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ባለስልጣን/ኢጋድ አባል አገራት ጋርም ለመስራት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል። በዚህም የህዝብ ለህዝብ ባህሉ ጠንካራ ለሆነባት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት በተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ገልጸው፤ ኤምባሲዎችና ዴፕሎማቶች ለገጽታ ግንባታና ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት የህዝብ ግንኙነት ስራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። በክልል ከተሞች ከሚገኙ ሆቴሎች መካከልም ለኢዜአ በስልክ በሰጡን መረጃ መሰረት ለክብረ በዓላቱ ለሚታደሙ እንግዶች ከወትሮው በተለየ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በቢሸፍቱ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ዋና ጸሃፊ አቶ ዘውዱ በላይ መስቀልን ጨምሮ በመጪው ሳምንት ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል ሆቴሎች ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ለአባላቱና ሰራተኞች መመሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል። ማኅበሩ 28 አባላት እንዳሉት ገልጸው፤ በቅድመ ዘግጅቱ ግን ከማኅበሩ አባላት ውጭ ያሉትን ሆቴልና ሪዞርቶችን ጨምሮ ምንም አይነት ችግር ሳይኖር የውጭ እንግዶች ቆይታቸው እንዲሰምር ልዩ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠውልናል። በአዋሳ የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ስራ አስኪያጅ አቶ እምሻው ተሾመ ከውጭ ለመጡ እንግዶች ደመራን በጋራ ለማክበር፣ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ የማድረግ ልዩ ዝግጅቶች ማድረጉን ተናግረዋል። ከዋጋ ቅናሽ በተጨማሪ የደመራ ክዋኔን በጋራ የማድረግ፣ የባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ፣ የቡና ስነስርዓት ዝግጅቶች እንዳሉም ገልጸዋል። በተመሳሳይ በባህር ዳር የሆምላንድ ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው ሆቴሉ ከመደበኛው ዋጋ ቅናሽ ማድረጉን፣ የአካባቢውን ወግና ባህል በጠበቀ መልኩ የምግብ አቅርቦት ማዘጋጀቱንና የደመራ ስነ ስርዓት በሆቴሉ አጸድ ማዘጋጁንም ገልጸውልናል።