ግብጽ በህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበችው ሃሳብ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ሉዓላዊ መብት የሚጋፋ ነው - የም/ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽ/ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ በህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበችው ሃሳብ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ሉዓላዊ መብት የሚጋፋ ነው - የም/ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽ/ቤት
መስከረም 15/2012 ግብጽ በአባይ ወንዝና በህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበችው ሃሳብ የኢትዮጵያን በወንዙ የመጠቀም ተፈጥሯዊና ሉዓላዊ መብቷን የሚጋፋ መሆኑን በናይል ትብብር መድረክ የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ገለጸ። ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የናይልን ወንዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በጋራ ለመጠቀም እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር መስከረም 2015 በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም አስር አንቀፅ ያለው የመርሆዎች ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል። ይሄንን ተከትሎም ከሶስቱም ሀገራት የተውጣጡ 15 የባለሙያዎች ቡድን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተው የደረሱበትን ውጤት ለውሃ ሚኒስትሮቻቸው አቅርበዋል። የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮችም መስከረም 2018 በአዲስ አበባ ለመወያየት ከተገናኙ በኋላ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ ቃለ ጉባኤውን ሳይፈርሙ ቀርተዋል። በሱዳን ተከስቶ በነበረው ቀውስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የሶስቱ ሀገራት ድርድርም በያዝነው መስከረም ላይ ሲቀጥል ግብጽ አዲስና ያልተጠበቀ ፕሮፖዛል ይዛ ቀርባለች። የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ግብጽ ያቀረበችው ሃሳብ ሶስቱ ሃገራት ከፈረሙት የስምምነት መርሆዎች ያፈነገጠ ነው። ግብጽ ያቀረበችው የእቅድ ሃሳብ ወይም ፕሮፖዛል "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" አይነት ራስ ወዳድነት የተንጸባረቀበትና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቷን የነፈገ ነውም ብለዋል። ብዙዎች እንደ ዓለም አቀፍ የውሃ ህግ የሚወስዱትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 1997 የወጣው ህግ በኢትዮጵያና ግብጽ በድምጸ ተዓቅቦ የጸደቀ መሆኑን አስታውሰዋል። ያልተፈረመና ያልጸደቀ ህግ አስገዳጅ ህግ ባይሆንም በዘልማድ ህግ ምክንያታዊና ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሁም በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳይ ያለማድረስ የሚሉ መርሆችን መከተል ለጋራ ልማት አስፈላጊ መሆኑን ግን አልሸሸጉም። ኢትዮጵያ የናይልን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ እስካሁን ድረስ የገባችበት ዓለም አቀፍ ህግ አለመኖሩን ገልጸው፤ በአባይ ወንዝ ላይ እንዳትጠቀም የሚከለክላት ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል የለም ብለዋል። ኢትዮጵያ በዓመት 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመልቀቅ ፈቃድኛ ናት እየተባለ በግብጽ በኩል የሚወጣው የተሳሳተ መረጃም የባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ እንጂ የኢትዮጵያ አቋም አይደለም ብለዋል። ይሄንን ግብጽ በዓመት እንዲለቀቅ ያቀረበችውን 40 ሜትር ኪዩብ ውሃ ለማግኘት ከሶስተኛ ወገን ጋር ለመደራደር ስትል የፈጠረችው ሃሳብ መሆኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለተፋፈሱ ሀገራት የምትከፍለው መስዋዕት እንጂ ግድቡን በሁለት ዓመት ሞልቶ የማጠናቀቅ ሙሉ መብት እንዳላትም ገልጸዋል። በታሪክ የናይል ወንዝ ዓመታዊ ዝቅተኛ ፍሰቱ 29 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ከፍተኛው ደግሞ 70 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ አካባቢ፣ አማካዩ ደግሞ 41 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መሆኑንም ጠቁመዋል አቶ ፈቅ አህመድ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ግብጽ ያቀረበችውን 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ብትፈቅድ ግድቡ ለመሙላት ዓመታትን ይወስዳል፤ ጭራሽ ላይሞላም ይችላል ብለዋል። ኢትዮጵያ ግብጽ ያቀረበችውን ሃሳብ የምትቀበል ከሆነ ወደፊት የማትወጣውን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላትም ገልጸዋል። "ለአብነትም ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ መሙላት የምትችለው ግብጽ በሯሷ የምትቆጣጠረው የአስዋን ግድብ የውሃ ሙሌት ከ 165 ሜትር በላይ ከሆነ ብቻ ነው" የሚለው ሃሳብም አደገኛ ነው ብለዋል። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግብጽ መሃንዲሶች እንዲያስተዳድሩት መጠየቅም የሀገርን ሉዓላዊነት መዳፈር ነው ብለዋል። ይህ ብቻ አይደለም" ውሃው ተፈጥሯዊ ፍሰቱን መጠበቅ አለበት" የሚለውም ሀሳብ ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት በወንዙ ተፋሰስ ላይ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ኑባሬ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑንም ገልጸዋል።