የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳያመጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳያመጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል - ምሁራን
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 15/2012 የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳያመጣ መንግስት ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ። በምዕራብ አፍሪካ ቀጣና የኦክስፋም ኢንተርናሽናል የፍትሃዊነት ፕሮግራም አማካሪ ሚስተር ክዌሲ ኦቤንግ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዋ ላይ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት እያደረገቻቸው ከሚገኙ ለውጦች መካከል የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግሉ ዘርፍ ማዘዋወር አንዱ ነው። ወደግሉ ዘርፍ ይዘዋወራሉ ከተባሉ መካከልም ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ የኃይል ዘርፍ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የስኳር ኢንዱስትሪ ይጠቀሳሉ። ኢኮኖሚውን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረግ የአገሪቱን ገቢ ሊያሳድግ እንደሚችል የተናገሩት ኦቤንግ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ በራሱ 'የዜጎችን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ አይችልም' ይላሉ። የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ውጤታማ እንዲሆን የመንግስት ድጋፍና የዘርፉም የስራ ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ የኢኮኖሚው ዕድገትና ትርፍ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ህዝብን ተጠቃሚ የማድረግ ተቋማዊ ጥንካሬም ይጠይቃል ብለዋል። መንግስት የግሉን ዘርፍ በመደገፍ፣ በመከታተልና በመቆጣጠር ኢኮኖሚው የአገሪቱን መሰረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት በቀጥታ የሚያረጋግጥ እንዲሆን ጠንካራ ስራ ይፈልጋልም ነው ያሉት። የኢኮኖሚ ምሁራኑ ዶክተር ሉሊት ምትኬና ዶክተር መሰለ ወልደማርያምም የህዝቡን ፍላጎት ሊመልሱ የሚችሉ ፖሊሲዎችን አብሮ በመቅረፅ ተደራሽ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ነው የገለጹት። በአገሪቱ የሚገኙ የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማትን ማጠናከርና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር መዘርጋትም ጊዜ የማይሰጠው ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። "ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎችን መርዳት ግዴታ ነው፣ ዜጎችን ማስተማር፣ የጤና ግልጋሎት መስጠት፣ ስራ ፈጠራ፣ ችሎታቸውን ማዳበር እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማዳረስ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ፣ ታክስ ላይ በጣም ሃብታም ከሆኑት እንዴት ወደ ሌሎች እንደሚሰራጭ ማሰብ ይኖርብናል" ያሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተመራማሪዋዶክተር ሉሊት ምትኬ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር መሰለ ወልደማሪያም በበኩላቸው "የተቋማት አቅምን መገንባት ነው ዋናው፣ ተቋማት ሲባል ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት፤ እስካሁን በወረቀት እየሰራን ነው ያለነው ሌላው ዓለም ደግሞ ትንሽ ወደ ቴክኖሎጂ ተሸጋግሯል ስለዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፤ ሽግግሩም ቴክኖሎጂን ያጣመረ መሆን አለበት ።" ሚስተር ክዌሲ ኦቤንግ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚው ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ለዜጎች ተደራሽ የሚሆንበትን ቅድመ ሁኔታ ሳይፈጥሩ ለግሉ ዘርፍ ክፍት በመሆናቸው ችግር እንደገጠማቸው አውስተዋል። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያም እንዳይከሰት 'ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል' ሲሉ አስገንዝበዋል። "ይህ ካልሆነ ግን ኢኮኖሚው ለብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን ጥቅም መዋልና በዜጎቹ መመራት ሲገባው በጣም ጥቂት በሆኑ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ቁጥጥር ስር ሊወድቅ ይችላል፤ ብዙ አገራት ስህተት የሚሰሩት እዚህ ላይ ነው በብዙ አገራት ኢ-ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚመጣው፤ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የሚመጣው ለዛ ነው። ለምሳሌ የበርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን ተሞክሮ መውሰድ እንችላለን ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ ብቻውን ለትርፍ እንጂ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ትኩረት የሚሰጥ ስላልሆነ ማለት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ስህተት ትምህርት ወስዳ በአግባቡ ልትመራው ይገባል" ብለዋል፡፡