ቀጥታ፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ የተከሰተ የእሳት ቃጠሎ አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

ሶዶ (ኢዜአ) መስከረም 15 ቀን 2012--- በወላይታ ሶዶ ከተማ የተከሰተ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ። ህብረተሰቡ በዝናብ ወቅትና በበዓላት ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጠቀም ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ አሳስቧል። በወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኢንስፔክተር ህያሁንሞጋ እንደገለጹት አደጋው የተከሰተው ትናንት ምሽት 7፡00 ሰዓት በመሃል ክፍለ-ከተማ በተለምዶ 21 ማዞሪያ በሚባል መንደር ነው፡፡ በአደጋውም የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ፣ ቶርኖ ቤት እና አንድ መለስተኛ ሻይ ቤት በውስጣቸው ከያዟቸው ንብረቶች ጋር መውደማቸውን አስረድተዋል። “የከተማው ነዋሪ፣ የጸጥታ ኃይሎችና የከተማው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ባደረጉት ርብርብ እሳቱ ወደሌላ አካባቢ ሳይስፋፋና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሏል” ብለዋል። እንደ ምክትል ኢንስፔክተር ህያሁን ገለጻ በአደጋው ከንብረት ውድመት ባሻገር በሰው ህይወትና አካል ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም። በአደጋው ምክንያት የደረሰው የውድመት መጠን ፖሊስ የማጣራት ሥራ እንደሚከናውንም አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ከፍተኛ ዝናብ እየጣለ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኢንስፔክተሩ ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጠቀም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም