በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ልማት አሁንም ትኩረት ያሻቸዋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ልማት አሁንም ትኩረት ያሻቸዋል ተባለ
መስከረም 14/2012 በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት እድገት ውስጥ የቱሪዝም ድርሻ እንዲያንሰራራ ለማድርግ የጉብኝት መዳረሻ ስፍራዎች ልማት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ። በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ ውስጥ የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ትኩረት ከተሰጠው አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ ነው። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛን ጨምሮ የተለያየ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ታሪካዊ ቦታዎች መገኛና ሌሎች የቱሪስት መስህቦች አሏት። ይሁን እንጂ ይህን እምቅ ሃብት ወደ ጥቅም ቀይሮ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና አገርን በማስተዋወቅ በኩል ብዙም እንዳልተሰራበት የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ። የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ልዑልሰገድ መሰለ ቱሪዝም በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ውስጥ ያለው ድርሻ እንዲያንሰራራ ከተፈለገ መሰረተ ልማት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ሊሆን ይገባል ይላሉ። ከቱሪዝም መስህብ በተጨባጭ ለኢኮኖሚ እድገቷ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የቱሪስቶችን ቆይታ የሚያራዝሙ አዳዲስ መርሃ ግብሮችም ሊታሰብባቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል። የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ልማትን ለአብነት በመጥቀስ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት በማቅረ በኩል በማህበሩ አማካኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የቱሪዝም ዘርፉ ብዙም የልተሰራበት መሆኑን በመግለጽ "ሙሽሪት ኢትዮጵያን" ለማስተዋወቅ መጀመሪያ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ማቋቋም መቻል አለብን ብለዋል። የቱሪዝም ፈንድ ማቋቋም ሌላው ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የሌሎች አፍሪካ አገራትን ልምድ አንስተው አጋርተዋል። ይህም ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሲመጡ ለተለያዩ ኤጀንሲዎች የሚከፍሉትን ዶላር አገር ውስጥ ማስቀረት እንደሚያስችል አስረድተዋል። የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አሁንም ቢሆን ከሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት መላቀቅ እንዳልቻለ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ማንኛውም ቱሪስት ለጎብኝት ሲዘዋወር ከሚስቡት ሁኔታዎች ውስጥ የማረፊያ ቦታዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ሃዲሰ ጥላሁን ናቸው። በመሆኑም ደረጃ ያላቸው በርካታ ሆቴሎችና ለቱሪስት አመች የሆኑ መሰረተ ልማቶች አለመሟላታቸው ዘርፉን ይጎዳዋል ብለዋል። የተሟላ አገልግሎት የሚያቀርቡ ሆቴሎች ያሉባቸው አገሮች በቱሪስቶች የበለጠ አመኔታና ተወዳጅነት አላቸው። በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃት ባለፉት 10 አመታት የግል ባለሃብቱ በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ማሳየቱን አንስተዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅና ቱሪዝም እንደ አንድ የእድገት ምንጭ ለመጠቀም የተያዘውን እቅድ እውን ለማድረግ በተሰማሩበት ዘርፍ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታችውንም ገልጸዋል። ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት፣ በመጓጓዣ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል፣ መሰረተ ልማት፣ የሚጎበኙ ቦታዎች ገላጭነትና ሳቢነት ከቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ልማት ውስጥ ይጠቀሳሉ።