በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ለሚገኙ ከ1 ሺህ 600 በላይ ችግረኛ ተማሪዎች ድጋፍ ተደረገ

አክሱም (ኢዜአ) መስከረም 13 ቀን 2012 ---በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አክሱም ከተማና ላዕላይ ማይጨው ወረዳ ለሚገኙ ከ1 ሺህ 600 በላይ ችግረኛ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ። ድጋፉ ወጣቶች በተነሳሽነት ካሰባሰቡት ሃብት የተገኘ መሆኑን የብሩህ ተስፋ ለተቸገሩ ተማሪዎች መርጃ ማህበር አስተባባሪ ወጣት ሃፍቶም አሰፋ ተናግሯል። አስተባባሪው እንዳለው በወጣቶች በጎ ፈቃድ የተመሰረተው ማህበር ለተቸገሩ ተማሪዎች ድጋፍ ያደረገው የአካባቢውን ማህበረሰብ እና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ነው። በእዚህም በአክሱም ከተማና ላዕላይ ማይጨው ወረዳ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 1 ሺህ 630 ተማሪዎች 40 ሺህ ደብተር እና ስምንት ሺህ እስክርቢቶ መከፋፈሉን ነው የገለጹት። ለተማሪዎቹ የተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ በገንዘብ ሲሰላ ወደ 300 ሺህ ብር የሚጠጋ መሆኑንም ወጣት ሃፍቶም ተናግሯል። ድጋፉን ለማድረግ በተዘጋጀ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የላዕላይ ማይጨው ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ አበባ ተስፋይ እንዳሉት ወጣቶች በተነሳሽነት ያከናወኑት መልካም ተግባር ሌሎችን የሚያስተምር ነው። "ሕብረተሰቡ ያሳየውን እርስ በእርስ የመተጋገዝ ባህል ለማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል" ብለዋል። ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ቁልፍ መሳሪያ ትምህርት በመሆኑ ተማሪዎች ጠንክረው መማር እንዳለባቸውም ዋና አስተዳዳሪዋ አስረድተዋል። ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል በወረዳው የሰግላሜን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሰለሞን ንጉሰ በበኩሉ ''የተደረገልን ድጋፍ በትጋት ትምህርታችን እንድከታተል ያግዘናል'' ብሏል። ልጃቸውን ለማስተማር አቅም እንደሌላቸው የገለጹትና ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ደግሞ በአክሱም ከተማ የደብረ ሰላም ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ አረፋይነ ናቸው። '' ማህበራዊ ችግሮቻችንን በጋራ መፍታት እንደሚቻል ወጣቶቹ አሳይተውናል፣ ተማሪዎቹ የትምህርት ድጋፍ ተደርጎላቸው ትምህርታቸው በአግባቡ እንዲከታተሉ መደረጉ የሚበረታታ ነው'' ብለዋል። በክልል ደረጃ ከትናንት በስቲያ በተጀመረው የ2012 የትምህርት ዘመን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም