ቀጥታ፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የድርሻውን እንዲያበረክት መንግስት ድጋፉን ያጠናክራል

መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም   (ኢዜአ) የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የድርሻውን እንዲያበረክት መንግስት ድጋፉን እንደሚያጠናክር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ። ''ኢትዮ-ኮን'' ዓለም ዓቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ትናንት በአዲስ አበባ ተከፍቷል። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ተቋራጫች ማሕበር 16ኛ ጊዜ ያዘጋጀው ''ኢትዮ-ኮን'' ዓለም ዓቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ሲከፈት እንደገለጹት፤ ዘርፉ በርካታ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መሰረተ ልማቶችን፣ ፋብሪካዎችንና የመኖሪያ ቤቶችንና ሌሎች ግንባታዎችን በማካሄድ ካስመዘገበው ውጤት በተጨማሪ ስራ አጥነትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ኢንጂነር አይሻ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ብዙ የሚጠበቅበት በመሆኑ የአገሮችን ተሞክሮ በመቀመር የማዘመን ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። በዘርፉ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት የልምድ ልውውጥ ለማድረግና እርስ በርስ በመቀራረብ ለመስራት መሞከር ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸዋል። መንግስትም ይህንን በመገንዘብ ዘርፉ የሚመራበት የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እያዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ተቋራጫች ማሕበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አምሃ ስሜ በበኩላቸው እስካሁን በተካሔዱት ኤግዚቢሽኖች የዘርፉ ተዋናዮች የንግድ ለንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ ማስቻሉን አስታውሰዋል። በተለይም ከውጭ ከሚመጡ የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ይዘው የሚያመጧቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ለመተዋወቅና የአገር ቤት አምራቾች ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። በዚሁ ኤግዚቢሽን ላይም በሚዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ በሚቀርበው የጥናት ወረቀት ችግር ፈቺ ውይይቶችን ለማድረግ የተቻለ መሆኑን ጠቁመዋል። ከኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች መካከል የቢቶር ኬሚካል ኢንዱስትሪ የግል ማሕበር የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ኃይለስላሴ ኤግዚቢሽኑ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል። ምርት ከማስተዋወቅ ባሻገር ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለመተዋወቅና ደንበኞትን ለማፍራት ወሳኝ እንደሚሆን ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከመተዋወቅ ባሻገር በየአመቱ ተጨማሪ ምርቶችን ለማስተዋወቅና  የተሻለ ገበያ ለማግኝት እየረዳቸው መሆኑን አቶ ዳንኤል አስረድተዋል። ሌላው የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊ አፍሮቻይና ኩባንያ ተወካይ አቶ እስመለአለም ምሕረቱ እንደሚሉት፤ የተለያዩ የውሃ ፓይፕ ምርቶችን እንደሚያስተዋውቁ ይናገራሉ። ምርቶቹ ከውጭ የሚመጡ በመሆኑም ለአገር ውስጥ ተቋራጮች በማቅረብና ለማስተዋወቅ ከተቋራጮች ጋር ለመገናኝትና የዘርፉን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ምርት ለማቅረብ ኤግዚቢሽኑን እንደተጠቀሙበት አመልክተዋል። ለአራት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ አለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ 174 የዘርፉ ተዋናዩች የተሳተፉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከቻይና፣ ቱርክ፣ ሕንድ፣ ጣሊያን እንዲሁም ከተባበሩት አረብ ኢሜሬት የመጡ ኩባንያዎች ተገኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም