ቀጥታ፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የኢንቨስትመንት ተቋማት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ ተጠቆመ

ፍቼ (ኢዜአ) መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በባለሀብቶች አየተካሄደ ያለው የኢንቨስትመንት ተቋማት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የኢንቨስትመንት ተቋማት ግንባታ ሥራው ከ5ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተመልክቷል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው የተቋማትን ግንባታ እያካሄዱ ያሉት 201 ነባርና አዲስ ባለሀብቶች ናቸው። በባለሀብቶቹ ግንባታቸው እየተፋጠነ ያለው የዘመናዊ ሆቴል፣ የሲሚንቶ፣ የቀለም፣ የአግሮ ኢንዱስትሪና የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ከ71 በመቶ በላይ የተጠናቀቀ ሲሆን የተወሰኑት በከፊል የማምረትና አገልግሎት መስጠት ሂደት ላይ መሆናቸውን ወይዘሮ አስቴር አስረድተዋል። እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በዘመናዊ ግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በተለያዩ የአገልግሎት ሥራ ዘርፎች ፍቃድ የወሰዱ 55 ባለሀብቶች የሚያካሂዱት ግንባታ ከ44 በመቶ በላይ መድረሱን አመልክተዋል። ባለሀብቶቹ ከ18 ወራት በኋላ የግንባታ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ ወደሥራ ለመግባት የውል ግዴታ መፈራረማቸውንም ተናግረዋል፡፡ እንደወይዘሮ አስቴር ገለጻ፣ በዞኑ ያሉ የኢንቨስትመንት ግንባታ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ከ1ዐሺህ በላይ ለሆኑ ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላሉ። በገቡት ውል መሰረት ግንባታ ካላካሄዱ 65 ባለሀብቶች 571 ሄክታር መሬት ተመላሽ ተደርጐ ከ4ሺህ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩበት መደረጉን አመልክተዋል። በተያዘው አዲስ ዓመት ከ15ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ለቱሪዝም፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለአገልግሎት መስጫዎች በማዘጋጀት ባለሀብቶችን ለመሳብ ጥረት እንደሚደረግም ወይዘሮ አስቴር አመልክተዋል። ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለባለሀብቶች በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ሲፖዚየምና የኢንቨስትመንት ፎረም እንደሚዘጋጅም አስታውቀዋል፡፡ በፍቼ ከተማ በሆቴልና ቱሪዝም ሥራ የተሰማሩት አቶ ግሩም ደበሌ በበኩላቸው ባለሀብቶች በስፋት ሊሰማሩባቸው የሚችሉ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች በአካባቢው እንዳሉ ጠቁመው የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ በኩል ብዙ ባለመሰራቱ የሚጠበቀውን ያህል እድገት እንዳልታየ ተናግረዋል፡፡ “ በቀጣይ የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ መሰረተ ልማቶችን መንግስትና ሕብረተሰቡ ቢያስፋፉ የአካባቢው እድገት እየተፋጠነ ይመጣል” ብለዋል። በውጫሌ ወረዳ የሚገኘው የጀማ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኤልሳቤት ገብሩ ለፋብሪካው የሚያስፈልግ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለማግኘታቸው በሙሉ አቅም ለመስራት መቸገራቸውን ተናግረዋል። የኃይል አቅርቦት አለመኖር ብዛት ያላቸው ሠራተኞችን ለመቅጠር እንቅፋት እንደሆነባቸውም ጠቁመው መንግስት ለችግራቸው መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡ በደገም ወረዳ ገንደ ሸኖ ከተማ በተቋቋመው የአቢሲኒያ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሥራ እድል ያገኘው ወጣት ፉፋ አድባሩ በበኩሉ የፋብሪካው መቋቋም ለእሱና በአካባቢው ላሉ 10ዐ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩን ነው የገለጸው። በአሁኑ ወቅትም በፋብሪካው በማሽን ጥገና ሙያ በመሰማራት በወር እስከ 1ዐሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ በማግኘት የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወት እየመራ መሆኑንኝ አመልክቷል። በሰሜን ሸዋ ዞን ከ1997 እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ አስር ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ 296 ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው የአካባቢውን ልማት በማፋጠን ላይ መሆናቸው ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም