ቀጥታ፡

ፀብን በፍቅር ያሸነፈዉን የጋሞ አባቶች ኩሩ ባህል ጠብቆ ማቆየት ይገባል---አቶ ርስቱ ይርዳው

ኢዜአ፤ መስከረም 13/2012 ፀብን በፍቅር ያሸነፈዉ የጋሞ አባቶችን ኩሩ ባህል ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ ፡፡ በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የዘመን መለወጫ "ዮ ማስቃላ" በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ፀብን በፍቅር ያሸነፈ የጋሞ አባቶችን ባህል መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

"በሀገራችን ከመጣው ለውጥ በተቃራኒ በተለያዩ አከባቢዎች የእርስ በእርስ ግጭት የሰብአዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉሶች ሲያጋጥሙ በጋሞ አከባቢ ሰላም መኖሩ ህዝቡን ያስተሳሰረው አገር በቀል ባህሉ ጠንካራ መሆኑን የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡

"ጥላቻን ወደ ፍቅር ፣ ፀብን ወደ ደስታ እርግማንን ወደ ምርቃት የቀየሩ ህዝቦች ባህል ክልላችንን ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ያኮራ ነዉ"ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጋሞ አከባቢ በቱሪዝምና ፍራፍሬ ሀብቶች እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ለአከባቢውና ለአገሪቱ ዕድገት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

የዞኑ ምሁራን ባህላዊ ትዉፊቶች ተጠብቀዉ ለትዉልድ ሊያስተላለፉና ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገዉ ጥረትም አዎንታዊ ድርሻቸውን ሊያበረክቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመስቀል በዓል የተጣሉት የሚታረቁበት ፣ በይቅርታ የሚደመሩበት ፣ ሰላምና እርቅ የሚፈጸምበት ልዩ የፍቅር መገለጫ በዓል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊና የአከባቢው ተወላጅ አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸዉ።

"የህዝቡን አንድነትና ህብረት የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች ለሰላምና ዴሞክራሲ ስርአት ያላቸው ድርሻ ጉልህ ነዉ" ያሉት ኃላፊው የጋሞ አባቶችን ኩሩ ባህል ወጣቱ ለመጪዉ ትዉልድ ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባም አሳስበዋል ፡፡

የጋሞ ዞን ተወላጅና በኢንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ዶክተር ታደሰ ወልዴ በበኩላቸዉ "ባህል ህይወታችንን ለማቃለል ከመርዳቱም በላይ ሳይንስን በመደገፍ ተኪ የሌለው ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

"በተመሳሳይም ኃይማኖት የመልካምነትና የደግነትን ልዕልና የሚያረጋግጥ በመሆኑ ህዝቡ ባህልና ኃይማኖቱን ጠብቆ ማቆየት የመጪው ትዉልድ ዋስትና ይሆናል" ነዉ ያሉት።

የመስቀልን በዓል በዞኑ የሚገኙ የጋሞ ፣የዘይሴና የግዲቾ ብሔረሰቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ በመሆን ለዘመናት ሲያከብሩት እንደኖሩ የተናገሩት ደግሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘዉዴ ናቸዉ።

"የህዝቡ አብሮነት መገለጫ የሆነው የመስቀል በዓል ሰላምን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ የሚያሳልጥ ነው"ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት በህዝቦች መካከል ያሉ አንዳንድ የፀረ-ሰላም ኃይሎችን አስተሳሰብ በመታገል አብሮነትን ሊያጠናክሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በበዓሉ ላይም የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በሃገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም