መንግስታትና የግሉ ዘርፍ መሪዎች በጉባኤው ላይ የገቡትን ቃል በፍጥነት በተግባር ላይ ማዋል አለባቸው- ተመድ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስታትና የግሉ ዘርፍ መሪዎች በጉባኤው ላይ የገቡትን ቃል በፍጥነት በተግባር ላይ ማዋል አለባቸው- ተመድ
መንግስታትና የግሉ ዘርፍ መሪዎች በፓሪሱ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የገቡትን ቃል በፍጥነት ተግባር ላይ ማዋል እንዳለባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጽሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አስታወቁ። አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመፍታት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። በባለድርሻ አካላቱ የተቀመጡት እቅዶች በሚፈለገው ፍጥነት ከተተገበሩ በጉባኤው ላይ መንግስታትና የግሉ ዘርፍ ዋንኛ ተዋናዮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ ለውጦች ማምጣት እንደሚቻል በጉባኤው ላይ ተገልጿል። በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የተባበሩት መንግስት ድርጅት የ74ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ትናንት መካሄዱ ይታወሳል። የተለያዩ አገሮች መንግስታት እና የግል ተቋማት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ የረጅም ጊዜ እቅዶችና የድርጊት መርሃ ግብሮችን በጉባኤው ላይ ይፋ አድርገዋል። 74ኛው የተመድ ጉባኤ እ.አ.አ በ2016 በተፈረመው የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እ.አ.አ በ2050 በዓለም ደረጃ የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ የየአገሮቹ መንግስታት፣ የቢዝነስ ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት የገቡትን ቁርጠኝነት ማጽናት ዋንኛ አላማ መሆኑን ገልጿል። በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ጭማሬ ከ2 ዲግሪ ሴሊሺየስ በታች እንዲሆን ማድረግና ከስምምነቱ በመነሳት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መንግስታት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በተመለከተ የሚያዘጋጇቸው ብሔራዊ እቅዶች የደረሱበትን ደረጃ በጉባኤው ላይ ይፋ አድርገዋል። በዓለም ላይ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ለመግታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከሶስት እስከ አምስት እጥፍ ማሳደግ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። መንግስታትና የግሉ ዘርፍ መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥንና የካርቦን ልቀትን ለመከላከል ይፋ ያደረጓቸውን እቅዶች ተመድ ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ባወጣው የፕሬስ መግለጫ ላይ አስቀምጧል። ቻይና የካርቦን ልቀት መጠንን በየዓመቱ በ12 ቢሊዮን ቶን ለመቀነስ እንደምትሰራ ቃል ገብታለች። የአውሮፓ ህብረት የ2020 የበጀቱን 25 በመቶ ለአየር ንብረት ለውጥ ስራዎች እንደሚያውል ቃል የገባ ሲሆን ፤ ሩሲያ ደግሞ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን በፓርላማዋ እንደምታጸድቅ ገልጻለች። ይህም ስምምነቱን በፓርላማቸው ያጸደቁት አገራት ቁጥርን ወደ 187 ከፍ ያደርገዋል። ፈረንሳይ ፖሊሲያቸው ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት የሚቃረን አገሮች ጋር ምንም አይነት የንግድ ስምምነት እንደማታድርግ የገለጸች ሲሆን፤ ጀርመን እ.አ.አ 2050 የካርቦን ልቀት መጠንን ዜሮ ለማድረስ እንደምትሠራ ቃል ገብታለች። በአየር ንብረት ለውጥ ዋንኛ ተጎጂ ለሆኑ አገሮች ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ይፋዊ የገንዘብ ማግኛ መንገድ ለሆነው ለአረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ በቅርቡ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡት አራት አገሮች በተጨማሪ 12 አገሮች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። እንግሊዝ እ.አ.አ ከ2020 እስከ 2025 ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብታለች። ህንድ እ.አ.አ በ2022 የታዳሽ የሃይል ተጠቃሚነቷን 175 ጊጋ ዋት ወደ 450 ጊጋዋት ለማሳደግ እንደምትፈልግም ገልጻለች። ፓኪስታን በቀጣይ አምስት ዓመታት ከ10 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዟን ገልጻለች። 77 አገሮች እ.አ.አ በ2050 የካርቦን ልቀታቸውን ዜሮ ለማድረግ እንደሚሠሩ በጉባኤው ላይ የገለጹ ሲሆን፤ ሌሎች 77 አገሮች ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግና የማሻሻያ ስራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል። 80 የሚሆኑት የህብረቱ አባል አገሮች በጸሐይ ሃይል ማመንጨት ዙሪያ የሚሰራውን ዓለም አቀፍ የጸሐይ ሃይል ጥምረትን ተቀላቅለዋል። የግሉ ዘርፍ ቁርጠኝነትን በተመለከተ በዓለም ላይ በድምሩ ከ2 ትሪሊዮን በላይ ኢንቨስትመንት ያላቸው ተቋማት እ.አ.አ በ2050 ሙሉ ለመሉ ከካርቦን ነጻ የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ውስጥ ለመግባት ቃል ገብተዋል። በዓለም ላይ 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር ካፓቲል ያላቸው 87 ኩባንያዎች የካርቦን ልቀት መጠናቸውን ለመቀነስ ቃል የገቡ ሲሆን፤ ሳይንቲስቶች የሚያደርጓቸውን ጥናቶችና ምክረ ሀሳቦች መሰረት በማድረግ የሚያከናውኗቸውን ኢንቨስትመንቶች ቃል ከተገባው ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች የሙቀት ጭማሬ ስራን በመስራት የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን መግለጫው አመልክቷል። የዓለም አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን የባንክ ኢንቨስትመንት የያዙ 130 ዓለም አቀፍ ባንኮች ስራቸውን ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦች ጋር ለማጣጣም እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በትናንቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ከ70 በላይ የካርቦን ልቀት መጠን ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥ ለመግታት የሚያስችሉ ማዕቀፎችና እቅዶች ይፋ መሆናቸውን ተመድ ገልጿል። በባለድርሻ አካላቱ የተቀመጡት እቅዶች በሚፈለገው ፍጥነት ከተተገበሩ ሁሉን አቀፍ ለውጦች ማምጣት እንደሚቻል ተመድ አስታውቋል። አገሮችና ተቋማት ከቃል አልፈው በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት እንዳለባቸው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትዬሬዝ መናገራቸውን መግለጫው አስታውሷል። ተመድ እ.አ.አ በ2015 በፓሪስ ላይ የተደረሰውን ስምምነት እንደ አሜሪካ እና አውሮፓ ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚ አመንጪዎች በገቡት ቃል መሰረት ስምምነቱን እየተገበሩት ባለመሆኑ የዓለም ሙቀት መጠን መጨመር እጅጉን እንዳሳሰበው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። የዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት በዓለም ዙሪያ ኢንዱስትሪው ከመስፋፋቱ በፊት ከነበረው የአየር ጠባይ ጋር ሲነጻጸር አሁን ያለው የዓለማችን ሙቀት በአንድ ዲግሪ መጨመሩን የገለጸ ሲሆን፤ በዚሁ ከቀጠለ እ.አ.አ በ2100 ላይ የዓለም ሙቀት ከ3-5 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ እንደሚጨምር ግምቱን አስቀምጧል። በተመድ 74ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከሶስት ቀናት በፊት በአየር ንብረት ላይ የሚሰሩ ወጣቶች ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን ወጣቶቹ አየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የተለያዩ መፍትሄዎችና ቴክኖሎጂዎችንም በዝርዝር ማቅረባቸው ይታወሳል። በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የቀጣይ ቀናት ቆይታ መሪዎች በሚያደርጓቸው ንግግሮች የግል ዘርፉ ተዋናዮች ይፋ የሚያደርጓቸው እቅዶች የሚጠበቁ ይሆናሉ።