የአፍረካ ሆቴልና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍረካ ሆቴልና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
ኢዜአ መሰከረም 13 /2012 የአፍረካ ሆቴልና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሆቴል ግንባታ ዘርፍ ያሉ ልምዶችን ለማየት አስችሏል። በኢትዮጵያ የጉባዔው አዘጋጅና የካሊብራ ሆቴል አማካሪ ስራ አስኪያጅ አቶ ነዋይ ብርሃኑ ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ጥሩ የትብብር ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል። ቀደም ብሎም ኢትዮጵያ ሁለት ተመሳሳይ ጉባኤዎችን ማስተናገዷ በኢትዮጵያ የሚገነቡ ሆቴሌች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ልምድ ለማግኘት አስችሏል ብለዋል። በተለይም በሆቴል ግንባታ ዘርፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ልምዶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት አግዟል። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ መለያ (ብራንድ) ያላቸው ሆቴሎች በኢትዮጵያ ሊከፈቱ የሚችሉበትን ሁኔታ እስከ ማመቻቸት ተደርሷል። ዓለም አቀፍ ብራንድ ካላቸው የሆቴል ባለቤቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር ካላቸው ዓለም አቀፍ ተደራሽነት አንጻር በኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰትንም እንዲጨምር እገዛ ያደርጋል። የምስራቅ አፍሪካ የራዲሰንብሉ ሆቴል ግሩፕ ምክትል ፕሬዝዳንት ቲም ኮርደን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በሆቴሉ ዘርፍ እድገት እያሳዩ ካሉ አገሮች አንዷ መሆኗን አንስተዋል። በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚደረጉ ጉባኤዎችም ኢትዮጵያ ያላትን አስደናቂ ውበት በመረዳት ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴል ባለቤቶች መዋለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ይረዳቸዋል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ልዑልሰገድ መሰለ ጉባኤው በተከታታይ በአዲስ አበባ መካሄዱ በዘርፉ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል። ቀደም ሲል በተካሄዱ ሁለት ጉባኤዎች ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው የሆቴል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያሉ አማራጮችን እንዲያጠኑ እድል መክፈቱን ገልጸዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እንዳሉትም ጉባኤው አፍሪካ ያላትን የሆቴልና ኢንቨስትመንት አመራጭ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል። አፍሪካ ሃይማኖት፣ ብርቅዬ እንስሳት፣ የተለያየ ባህልና ሌሎች የቱሪዝም አማራጮችን በአግባቡ ለመጠቀም ውጤታማ ፖሊሲዎችን መተግበር እንደሚገባትም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ዘርፉ ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገትና ለህዝቦች ተጠቃሚነት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ቅድሚያ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፍች አንዱ መሆኑን አስረድተዋል። መሰረተ ልማት ማሟላት፣ ለጎብኝዎች የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስፋትና ማልማት በዘርፉ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በሆቴል ዘርፍ መዋለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመደገፍም መንግስት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ ብዙ ሊያሰራ የሚችል የቱሪዝም ሃብት ያላት መሆኗ፣ አመቺ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መኖር፣ የሰው ሃይል መኖርና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል። በጉባኤው ከ450 በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ መለያ ያላቸው ሆቴል አስተዳደሪዎች፣ ለሆቴል ኢንቨስትመንት ፋይናንስ የሚያቀርቡ ተቋማት፣ በሆቴል ዘርፍ መዋለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፈቃደኛ የሆኑ ባለሃብቶች፣ ዓለም አቀፍ የሆቴል አማካሪዎች እየተሳተፉ ነው። የአፍሪካ ሆቴልና ኢንቨስትመንት ጉባኤ ነገም የሚቀጥል ሲሆን በዘርፉ ያሉ አማራጮች፣ ችግሮችና መፍትሄዎች እንዲሁም የልምድ ልውውጦች እንደሚካሄዱበት ይጠበቃል። የመጀመሪያውን የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም የተካሄደው እ.ኤ.አ. በ2011 በሞሮኮ ዋና ከተማ ካዛብላንካ ያስተናጋጅነት ነበር። በዓመቱና በተከታዩ በኬንያ፣ ናይሮቢ ሲካሄድአዲስ አበባ ከኖይሮቢ በመረከብ ሁለት ጊዜ በተከታታይ አስተናግዳለች፣ አሁን ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ እድሉን አግኝታ ማስተናገድ ችላለች።