ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ለሶስት ቀናት በሀዋሳ ከተማ የሥራ ጉብኝት

ኢዜአ መሰከረም 13 /2012 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ከመስከረም 7 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል። የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘውን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍና ራዕይ ተከትሎ በኮሚሽኑ ውስጥም ስለሚደረገው የለውጥ መርሃ-ግብር ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ለማድረግ መሆኑን ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ኮሚሽነሩ በሐዋሳ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ እስረኞችንና አያያዛቸውን ጐብኝተዋል። ዋና ኮሚሽነሩ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ የክልሉ ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሚዲያ ጋር ተወያይተዋል። ከሐዋሳው ጉብኝት ቀደም ብሎ በግጭት ከተጐዱ ቤተሰቦች ጋር የተወያዩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ "በግጭቱ የተጐዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በተገቢው መጠን ከመርዳት እና መልሶ ከማቋቋም በተጨማሪ የምርመራው በፍጥነት መጠናቀቅ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል፡” ብለዋል። ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ሌሎች ምንጮችም በተገኘው መረጃ መሠረት እስከ አሁን በተደረገው የፖሊስ ምርመራ፤ በሶስት ማዕከሎች በእስር ይገኙ ከነበሩ ወደ 1 ሺህ 500 ገደማ እስረኞች ውስጥ ከግማሽ በላይ የተለቀቁ መሆኑን መረዳት ተችሏል። ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ በጋራ እያካሄዱ ባሉት የምርመራ ሥራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ማስቻሉ ጥሩ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን "ለችግሩ መነሻ የሆነው ዋነኛ ምክንያት በሲዳማ ዞን ምክር ቤት ለቀረበው የክልልነት ጥያቄ በሚመለከታቸው አካላት ሲሰጥ የነበረው ምላሽ ወቅታዊ እና ስልታዊ አለመሆንና በሌላ በኩል ጥያቄውን በተናጠል ውሳኔ እና በኃይል ጭምር ለማስፈፀም የፈለጉ ቡድኖች ባራመዱት አስተሳሰብ የተነሳ በተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት እና ቀውስ ነው" ብለዋል ዶክተር ዳንኤል። አሁንም በህዳር ወር 2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ከታቀደው ሕዝበ-ውሳኔ አስቀድሞ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ማዕቀፎች በማዘጋጀት፣ እንዲሁም ተአማኒ በሆነ የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስቀድሞ መግባባት ላይ በመድረስ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር እጅግ አፋጣኝ እርምጃ ይሻል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ አበክረው አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን በአዲስ መልክ በማደራጀት እና በማጠናከር ነጻ የሰብዓዊ መብት ተቋም አድርጐ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በየደረጃውና በየክልሉ የሚደረገው ምክክር እንደሚቀጥልም ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም