በኢትዮጵያ አንድነትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮችን እንታገላለን - የእስልምና ዕምነት ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አንድነትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮችን እንታገላለን - የእስልምና ዕምነት ተከታዮች
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በኢትዮጵያ አንድነትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮችን በመታገል የሰላም ጥረቱ አካል በመሆን ሚናቸውን እንደሚወጡ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች አረጋገጡ። 1ሺህ439ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል እየተከበረ ነው። አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእምነቱ ተከታዮች እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ስጋት መቃለሉ አስደስቷቸዋል። ከሶስት ዓመት በፊት በሰላም ለመስገድ ችግር እንደነበር የተናገሩት ምዕመናኑ ዛሬ ያለው የሰላም አየር ዘላቂ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች ለአገራዊ ሰላም መረጋገጥ እንደሚሰሩ አብራርተዋል። በአገሩቱ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚሰሩ የተናገሩት ምዕመናኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የረመዳን ወር ሲጀመርና ሲጠናቀቅ ለህዝበ ሙስሊሙ ያስተላለፉት መልዕክት ህዝባዊ አንድነትን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።