ቀጥታ፡

ዲኤችኤል ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለውን የሎጂስቲክ አገልግሎት ጥራት ያለውና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

ኢዜአ መስከረም 13 / 2012 ዓ ም ዓለም አቀፉ የመልዕክት አስተላላፊና የጭነት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ የሆነው ዲኤችኤል በኢትዮጵያ ያለውን የሎጂስቲክ አገልግሎት ጥራት ያለውና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ። የዲኤችኤል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሎጅስቲክ አገልግሎት የጋራ ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ መግባቱን አስመልክቶ የተዘጋጀ ስነ ስርአት ትናንት ማምሻውን በቦሌ ስካይላይት ሆቴል ተካሄዷል። ዲኤችኤል ኩባንያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ14 ወራት በፊት በአፍሪካ ትልቁ የሎጅስቲክ አገልግሎት አቅራቢ መሆንን አላማ በማድረግ የጋራ ኩባንያ ለማቋቋም የሽርክና ስምምነት ተፈራርመው ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለው ህግ በሎጅስቲክ ዘርፉ የውጭ አገር ኩባንያዎች እንዳይሳተፉ የሚከለክል በመሆኑ የጋራ ኩባንያውን ለማቋቋም ጊዜ የወሰደ ጉዳይ እንደነበርም ይታወቃል። መንግስት የሎጅስቲክ አገልግሎት ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንዲሆን የህግ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ የጋራ ኩባንያው ፈቃድ አግኝቶ ላለፉት አራት ወራት በፕሮጀክት ደረጃ የሎጅስቲክ አገልግሎት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። የኢትዮጵ አየር መንገድ በሽርክናው የ51 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ያለው ሲሆን ዲኤችኤል ኩባንያ 49 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በመያዝ 'የዲኤችኤል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሎጅስቲክ አገልግሎት' በሚል መጠሪያ የጋራ ኩባንያ ተቋቁሞ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት አጠናቋል። የዲኤችኤል ኩባንያ ከሰሀራ በታች አገራት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ፕራሞድ ባጋልዋዲ እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡና ወደ ውጭ ሲላኩ ዋነኛው ጉዳይ የሎጅስቲክ አገልግሎት ነው። አገልግሎቱ ፈጣንና ብዙ ወጪ የማያስወጣ መሆን እንዳለበት አመልክተው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር በሎጅስቲክ አገልግሎት መመዘኛ 131 ደረጃ ላይ እንደምትገኝና የሎጅስቲክ አገልግሎት ጥራትና ፍጥነት ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። የሎጅስቲክ አገልግሎቱ ጊዜ የሚወስድና ብዙ ወጪ የሚያስወጣ መሆኑ፣ ከሌሎች የሎጅስቲክ አገልግሎት ከሚሰጡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለው ትስስስር ደካማ መሆንና ወቅቱ የደረሰባቸው የሎጅስቲክ ቴክኖሎጂዎች አለመኖራቸው ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ገልጸዋል። ዲኤችኤል ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጋራ ሲሰራ በኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አስቦ እንደሆነ ሚስተር ፕራሞድ ያስረዱት። "ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ አገር በቀል መፍትሄ" በሚል መርህ ኩባንያው ያለውን እውቀት ልምድ ቴክኖሎጂ የአሰራር ስርአት ወደ ኢትዮጵያ  በመምጣት በአገር በቀል ሀብት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የሎጅስቲክ ባለሙያዎችን ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳና ቱርክ ሄደው ኩባንያው ለ24 ሰአት የሚጠቀምበት ዘመናዊ የኦፕሬሽን ስርአት ላይ ስልጠና ወስደው የሎጅስቲክ ችግርን ከአገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እንዲፈቱ አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች በሎጅስቲክ አገልግሎት መገናኘት የሚያስችላት የኩባንያው የኦንላይን ቴክኖሎጂ ስርአት ውስጥ መግባቷ ከተለያዩ አገሮች ጋር ያላትን ትስስር እንደሚያጠናክረው ሚስተር ፕራሞድ ጠቅሰዋል።  የዲኤችኤል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሎጅስቲክ አገልግሎት የጋራ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ካሳ ኩባንያው የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን በቦሌ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክና በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መክፈቱን ገልጸው፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም በሞጆ የደረቅ ወደብ አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ ጣቢያ ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል። በአሁኑ ሰአት 26 ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ያሉት የጋራ ኩባንያው የሰራተኞቹን ቁጥር በሁለት እጥፍ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ አየር መንግድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በበኩላቸው አየር መንዱ ከዲኤችኤል ጋር ሽርክና የመሰረተው ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው መስክ እየሰራች ያለችውን ስራ ለመደገፍና የሎጅስቲክ ዘርፉን አቅም ለማሳደግ እንደሆነ ገልጸዋል። ዲኤችኤል ኩባንያ ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ አገር ውስጥ የሚገኙ ምርቶች ያሉትን የሎጅስቲክ አገልግሎት ችግሮች እንዲፈቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የጋራ ኩባንያው በመቐለ፣ ኮምቦልቻና ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቢሮዎችን በመክፈት በፓርኮች ውስጥ ያሉ አምራቾች በሎጅስቲክ ጉዳይ ላይ እንዳይጨነቁና እንዳያስቡ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራም አመልክተዋል። ዲኤችኤል ጥራት ያለው የሎጅስቲክ አገልግሎት ለመስጠት እቅድ መያዙን ነው አቶ ተወልደ ያስረዱት። መቀመጫውን በጀርመን ቦን ከተማ ያደረገው የዲኤችኤል ኩባንያ ከ220 በላይ አገሮች የሎጅስቲክ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን ኩባንያው በስሩ ከ550 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ያስተዳድራል። በአፍሪካ ትልቁ የጭነት አገልግሎት ሰጪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ክለሳ ባደረገበት የ2035 ራዕይ በ12 የካርጎ መስጫ አውሮፕላኖች በ65 መደረሻዎች በዓመት የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የጭነት አገልግሎት ለመስጠት አቅዷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም