ዘላቂ ሰላምና እድገት ማስመዝገብ የሚችል አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች እንዲመረጡ እናድርጋለን - ኢሰማኮ - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምና እድገት ማስመዝገብ የሚችል አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች እንዲመረጡ እናድርጋለን - ኢሰማኮ
መስከረም 13/2012 በኢትዮጵያ ቀጣይ በሚደረገው ብሄራዊ ምርጫ ዘላቂ ሰላምና እድገት ማስመዝገብ የሚችል አጀንዳ ያላቸው ፓርቲዎች እንዲመረጡ ግፊት እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ገለጸ። የሰራተኞችን መብትና ጥቅም የሚያከብርና የሚያስከብር፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥበቃ የሚያደርግ ፓርቲ እንዲመረጥ እድሉን እናመቻቻለንም ብሏል። የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ሰራተኞች በቀጣይ ብሄራዊ ምርጫ ላይ የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር መክሯል። የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ የፖለቲካ ምህዳሩ አሳታፊ እየሆነ መጥቷል። ለአብነትም በተለያዩ ሀገራት የነበሩትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከ 137 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት እንደ አንድ ማሳያ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ቀጣዩ ብሄራዊ ምርጫም ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ፣ ያሸነፈው ፓርቲም በሰላም ስልጣን እንዲይዝ፣ ከሌሎች የሲቪክ ማህራት ጋር እንሰራለንም ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም የኢትዮጵያን ሰራተኞች መብትና ጥቅም ከማስከበርም ባለፈ የሰላም ዋጋን የተረዳና በሀገሩ ደህንነት ላይ የማይደራደር ትውልድ እንገነባለን ብለዋል። የኮንፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አያሌው አህመድ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የሲቪክ ማህበራት አንድን ፓርቲ መደገፍም ሆነ የሰራተኞች ፓርቲን መመሰረት አይችሉም ብለዋል። ይሁን እንጂ የሰራተኞችን ብሎም የዜጎችን መብት በሚያስከብርና ሀገሪቱን ለዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበቃ ፓርቲ እንዲመረጥ ግፊት እናደርጋለን ብለዋል። የኮንፌደሬሽኑ ከ750 ሺህ በላይ አባላትም የስራ እድልን የሚፈጥር፣ በሰላም ላይ የማይደራደርና ድህነትን ማስወገድ የሚችል ፖሊሲ ያለውን ፓርቲ እንዲመርጡም አሳስበዋል። ሰራተኞችም የሚመርጧቸው ፓርቲዎች ኢንቨስትመንትን፣ ሰላምን፣ የስራ እድል ፈጠራን፣ የሰራተኞችን ጥቅማጥቅም ማስከበር፣ የመደራጀት መብት መፍቀድና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበር የሚችሉበት አጀንዳ እንዳላቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ለዚህም በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ያሉ ሰራተኞች የመምረጫ መስፈርታቸውን የሚለዩበት መድረክ እናዘጋጃለን ነው ያሉት።