ቀጥታ፡

በዞኑ በመንገድ መበላሸት ምክንያት መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

መስከረም 13 / 2012  (ኢዜአ) የመንገድ መበላሸት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር እያስከተለባቸው መሆኑን በሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አንዳንድ የሆሮ ቡሉቅ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡ በሆሮ ቡሉቅ ወረዳ የሰቀላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አስቻለች ጌቱ በሰጡት አስተያየት ከሻምቡ ከተማ - ጃርደጋ ጃርቴና አሙሩ ወረዳዎች የሚወስደው የጠጠር መንገድ በከፍተኛ ሁኔታ ተበላሽቷል፡፡ በተለይም ከሻምቡ ከተማ - ሆሮ ቡሉቅ ወረዳና ሰቀላ ከተማ መካከል ያለው መንገድ ለትራንስፖርት አስቸጋሪ በሆነ መልኩ በመበላሸቱ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተጽኖ መፍጠሩን ተናግረዋል ፡፡ በመንገዱ መበላሸት ምክንያት በሆሮ ቡሉቅ ወረዳ ሻምቡ ከተማ - ሰቀላ ከተማ ለመጓዝ 10 ብር የነበረው የትራንስፖርት ዋጋ 50 ብር መግባቱን አስታውቀዋል፡፡ በተበላሸው መንገድ አብዛኛውን ጊዜ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደማይሰጥ የገለፁት አስተያየት ሰጪዋ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መኪናዎች መንገደኞችን በቅብብሎሽ እንደሚያመላልሱ ተናግረዋል፡፡ አማራጭ ሲጠፋም ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች ጭምር ሕፃናትን አዝለው በእግራቸው ለመጓዝ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል፡፡ከመንገዱ መበላሸት የተነሣ 10 ብር የነበረው የትራንስፖርት ክፍያ አሁን 50 ብር ገብቷል ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ ዘውዴ ረጋሣ ናቸው፡፡ መኪናው በጭቃ ተይዞ 3 ቀን መንገድ ላይ ማደራቸውን የተናገሩት አሽከርካሪው አቶ ኦልያድ አዱኛ በበኩላቸው በመንገዱ መበላሸት ምክንያት መኪናቸው በየጊዜው በጭቃ እየተያዘ በሲኖትራኮች ተጎትቶ እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጭቃ ተይዘው በየመንገዱ እያደሩ መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዞኑ የመንገዶች ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቦደና ረጋሣ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  በመንገዱ መበላሸት ምክንያት በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መንገዱ የሚተዳደረው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በመሆኑ አስፈላጊው ጥገና እንዲደረግለት በተደጋጋሚ ጠይቀው መልስ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል ፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የነቀምቴ ቅርንጫፍ የኮንትራት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሌሊሣ ወልቀባ በሰጡት አስተያየት ችግሩ የተከሰተው መንገዱን ለመጠገን ኮንትራት የወሰደው 'ክራፍትስ' የተባለው የግል ድርጅት ከአቅም ማነስ ምክንያት መንገዱን በወቅቱ ባለመጠገኑ  ነው፡፡ አሁን የተፈጠረውን ችግር ለማቃለል ማሽነሪዎች ወደ አከባቢው ቢላኩም ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጥገና ስራውን ለማካሄድ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡ ዝናቡ እየቀለለ ሲመጣ ግን ሙሉ ጥገና ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም