የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆን ተገቢውን የህክምና እያገኘን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆን ተገቢውን የህክምና እያገኘን ነው
መስከረም 13 ቀን 2012 (ኢዜአ) የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆን ተገቢውን የህክምና እያገኙ መሆናቸውን በሀድያ ዞን አንዳንድ የአንሌሞ እና ሌሞ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በዞኑ የአንሌሞ ወረዳ ደቡብ ፎንቆ ነዋሪው አርሶ አደር ሻፊ ሱሊቶ ለኢዜአ እንደገለጹት የማህበረሰብ ጤና መድህን አባል የሆኑት ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ በየዓመቱ 205 ብር በመክፈል በእርሳቸውና በአምስት ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰውን የጤና እክል ያለምንም ሀሳብ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የህክምና አገልግሎት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የቤተሰብ አባላቸውም ሆነ እርሳቸው የጤና እክል በሚገጥማቸዉ ወቅት መታከሚያ ገንዘብ በማጣት ለተጨማሪ ችግር ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የማህረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል ከሆኑ በኋላ ያለምንም ስጋት እርሳቸዉንም ቤተሰቦቻቸዉንም ተገቢዉን የህክምና አገልግሎት እያገኙ እንደሆነም አስታዉቀዋል፡፡ በዚሁ ወረዳ ላይኛው ፎንቆ ቀበሌ በፍንቆ ጤና ጣቢያ ልጃቸዉን በማሳካም ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ በለጠች አለሙ በበኩላቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆናቸው የገንዘብ ጉዳይ እንደማያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡ በሳቸውም ሆነ በቤተሰባቸው ላይ የጤና ችግር ሲያጋጥም ተገቢውን የህክምና እርዳታ ከተቋማቱ እንደሚያገኙም ገልጸዋል፡፡ ያሉበት የጤና ሁኔታ በየወቅቱ ክትትል እንደሚፈልግ የተናገሩት ደግሞ በሌሞ ወረዳ የጀዌ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አዲሴ ቤይካሶ ናቸው፡፡ ያለባቸው ከፍተኛ የጤና ችግር ክትትል በማድረግ ረገድ በሌሎች የህክምና ተቋማት የሚፈለገውን ገንዘብ አውጥተው በግል አቅማቸው ህክምና ለማድረግ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ "በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የሚሰጠን የህክምና አግልግሎት ድጋፍ እንጂ ክፍያ አይደለም" ብለዋል፡፡ የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሊጂሶ በበኩላቸዉ በዞኑ ባሉ ሰባት ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በዞን ደረጃ 119ሺ 49 ቋሚ አባላት እንዳሉና በበጀት አመቱ የአባልነት ምጣኔውን ከፍ ለማድረግ 5 ሺህ 443 አዲስ አባላት መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡን በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር ብቁ የሰዉ ኃይል ተመድቦ እየተሰራ ቢሆንም በዞኑ የሚጠበቀውን ያክል ውጤታማ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ባለማከናወናቸው እቅዱ ስኬታማ እንዳልሆነ መገምገሙን በመጠቆም ለቀጣይ አመት ውጤታማ ስራ ለመስራት አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡