የተጋነነ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የተጋነነ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) መስከረም 12/ 2012 የተጋነነ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ክፍያ እንድንከፍል ተዳርገናል ሲሉ አንዳንድ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ እመቤት ወርቁ እንዳሉት በከተማው የኤሌክትሪክ ኃይል የደንበኞች አገልግሎት ቁጥር አንድ ማዕከል ሠራተኞች ቤት ለቤት መጥተው ቆጣሪ በማንበብ ክፍያቸውን ያሳውቋቸው ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደቤት ሳይመጡ በግምት በሚወሰንላቸው ክፍያ ከግንቦት እስከ ሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ከ800 እስከ 5 ሺህ ብር ያለአግባብ እንዲከፍሉ መደረጋቸውን ገልጸዋል። “የማዕከሉ ሠራተኞች ችግሩን በአካል ተመልክተው እንዲፈቱልኝ በተደጋጋሚ ባመለክትም መፍትሄ ባለማግኘቴ ለእንግልትና ለከፋ ችግር ተጋልጪያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 06 ነዋሪ አቶ አለሙ ዘውዴ በበኩላቸው “በኢትዮጵያ የኤሌትሪክ አገልግሎት የደብረ ብርሃን ዲስትሪክት አሰራሩን አዘምኛለሁ ቢልም ለባሰ መጉላላትና እንግልት ተዳርገናል” ብለዋል። “ወርሃዊ የመብራት ፍጆታ ለመክፈል እስከ ሁለት ቀን ተራ በመያዝ በመደበኛ ሥራችን ላይ ጫና አሳድሮብናል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢው መንግስት ችግሩን ፈትሾ በፍጥነት እንዲያስተካክልላቸው ጠይቀዋል። ለመኖሪያ ቤት ለሚጠቀሙበት 5 አምፖል ብቻ ከግንቦት ወር ጀምሮ 4 ሺህ 900 ብር እንዲከፍሉ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ በከተማው ቀበሌ 04 የሚኖሩት አቶ ጌታቸው ፍቅረ ናቸው። “ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ባመለክትም ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ ከመጉላላት ውጪ ሰሚና ምላሽ የሚሰጥ አካል አላገኘሁም” ብለዋል። በኢትዮጵያ የኤሌትሪክ አገልግሎት የደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ በበኩላቸው በነዋሪዎች የቀረበው ቅሬታ አግባብ መሆኑን አምነው ችግሩ አሰራሩን ለማዘመን በተደረገ ለውጥ መፈጠሩን አስረድተዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ሠራተኞች በቴክኖሎጂ ወደ ተደገፈው አዲሱ አሰራር ፈጥነው መግባት አለመቻላቸው ለችግሩ አንድ ምክንያት ነው፣ “በቀጣይ ከነዋሪዎች ለቀረበው ቅሬታ ማጣራት ተደርጎ ተገቢ ምላሽ ይሰጣል” ብለዋል። ሕብረተሰቡ መንግስት የተሻለ አሰራር እንዲዘረጋለት ሲጠይቅ በኔትወርክ መቆራረጥና በሠራተኛ እጥረት ሳቢያ ለሌላ ችግር አንዲጋለጥ ማድረግ አግባብ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የሰው ኃይልን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በቆጣሪ አንባቢዎች ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገናል የሚል ቅሬታ ከደንበኞች እንደቀረበላቸው የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ ችግሩን ለማቃለል ከማጣራት ስራ በተጨማሪ ባለሙያዎች ከቆጣሪው ያነበቡበትን በካርድ መዝግበው ለደንበኞች የሚሰጡበት አሰራር በቅርቡ እንደሚጀመር አስረድተዋል። ማዕከሉ ከ12 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።