ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ልማት በትኩረት ትሰራለች -- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 12/2012 ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ልማት በትኩረት ከመስራት ባለፈ ዓለምን ከአየር ንብረት ለውጥ ጥፋት ለመታደግ በሚደረገው ዓለም ዓቀፍ ርብርብ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ተናግረዋል። ሚኒስትሩ በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 74ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በፎርድ ፋውንዴሽን ኤነርጂ አክሽን ፎረም መክፈቻ ላይ በመገኘት የጉባዔውን የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። ኢትዮጵያ የኢነርጂ ሽግግር  ስትራቴጂ ነድፋ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ለማሰለፍ እየሰራች መሆኑን ማስረዳታቸውንም ነው ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው ጋዜጣዊ ያስታወቀው። በሂደቱም የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ የመሄድን የትግበራ አቅጣጫ እየተከተለች መሆኗን መግለጫው ያመለክታል። የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራም ተገቢውን ትኩረት እንዲሠጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ  ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ኢትዮጵያ “ትብብር ዘላቂ የሃይል ልማት ለሁሉም”  ጥምረት ውስጥ አባል በመሆን ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኗን አስታውቀዋል። በዚሁ መድረክ ንግግር ያደረጉት የዴንማርኩ የአየር ንብረትና የኤነርጂ ሚኒስትር ዳን የርገንሰን ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳን በአርአያነት እየመራች ያለች ሃገር መሆኗን በማንሳት አድናቆታቸውን ገልፀዋል ። ኢትዮጵያ ከዴንማርክ ጋር በመሆን የከፍተኛ ባለስልጣናት የአየር ንብረት ለውጥ የድርጊት መርሀ ግብርን በጋራ የምትመራው ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም