ቀጥታ፡

የቴሌኮም አገልግሎት ወርሃዊ ክፍያን በባንከ መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 12/2012 ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች የቴሌኮም አገልግሎት ወርሃዊ ክፍያን በኢትዮጵያ ንግድ ባንከ መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱን በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ፕሬዝዳንቱ አቶ ባጫ ጊና ፈርመዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ከመጪው መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን የሚፈፅሙት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ሂሳባቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ መፈጸም የሚችሉ መሆኑም ታውቋል። በስምምነቱ መሰረት ደንበኞች ለተጠቀሙበት አገልግሎት በሲ.ቢ.ኢ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግ፣ በኢንተርኔት ባንኪንግና በኤቲኤም መክፈል ይችላሉ። ደንበኞች በቀጥታ የባንክ ማዘዣ በባንኩ ቅርንጫፎች በአካል በመገኘት ክፍያቸውን መፈጸም የሚችሉም ይሆናል። ከባንኩ አማራጮች በተጨማሪ ደንበኞች በአቅራቢያቸው በሚገኙ በኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከላት፣ በአጋር የንግድ ማዕከላትና በይሙሉ ኤሌክትሪክ አየር ሰዓት መሙያ ወርኃዊ ሂሳባቸውን መክፈያ የሚችሉባቸው አማራጮች ናቸው። ኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግና የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት በርካታ የማሻሻያ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም