ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ሥራዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት - ተ.መ.ድ

መስከረም 12/2012 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን የልማት ሥራ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር ተወካይ ቱርሃን ሳለህ ገለጹ። የዓለም የሠላም ቀን ‘የአየር ንብርት ጥበቃ ሥራዎች ለሰላም’ በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል። በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር ተወካይ ቱርሃን ሳለህ እንደተናገሩት፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራና የሰላም ሁኔታ በእጅጉ የተያያዙና ተኩረት የሚሹ ናቸው። በአየር ንብረት ለውጥ የሚያባብሱ ማኅበራዊ ቀውሶች በተለይም የኃብት መቀራመት በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የዘለቀውን አብሮነትና የመቻቻል መንፈስ ያደፈርሳል ነው ያሉት። የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትለውን ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተወካዩ ገልጸዋል። ይህም በአገር አቀፍና በዓለም ደረጃ ዘላቂ ልማትና ሰላም ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የሚባል የአየር ንብረት ጥበቃ ስትራቴጂ ቀይሳ ወደ ሥራ መግባቷን ያስታወሱት ቱርሃን ይህንንም አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አሳስበዋል። በመድረኩ ላይ የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነን ወክለው መልክት ያስተላለፉት አቶ አደፍርስ ወርቁም የሰላምና የአየር ንብረት ተዛምዶ ጥብቅ መሆኑን አብራርትዋል። ቀደም ሲል የተካሄዱ ጥናቶች "ሰላምና የአየር ንብረት ተዛምዶ ቀጥተኛ አይደለም" የሚሉ ቢሆንም አሁን ላይ በርካታ ጥናቶች ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው አሳይተዋል ብለዋል። ድርቅና መሰል የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣቸው ችግሮች ለበርካታ ሰዎች መፈናቀልና መሰደድ ምክንያት በመሆን በሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጥገኛ የመሆን እድል ይፈጥራል። በአከባቢው ያሉ የተፈጥሮ ኃብት መመናመን ሲገጥም ሰዎች ወደ መቀራመት እንደሚገቡ ጠቁመው ይህም የኋላ ኋላ ግጭት ውስጥ እየከተታቸው መሆኑን አስረድተዋል። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም የአየር ንብረት ለውጥን ለመመከት በሌላ በኩል ዘላቂ ልማት ለማፋጠን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። የልማት ሥራዎች አከበቢን እንዳይጎዱ ማድረግና የግብርና ሥራዎችም የአየር ንብረት ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን ያጠቃልላል ብለዋል። ይህም በቀጥታ ከተፈጥሮ ኃብት መጓደል የሚመነጨውን የሰላም እጦት ከመሰረቱ ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም