ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሠላምን ለማረጋገጥ በግጭት መንስዔዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን ገለጸች

መስከረም 12/2012 የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሠላምን ለማረጋገጥ በግጭት መንስዔዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗን አስታወቀች። ቤተ ክርስቲያኗ በኢትዮጵያ የሠላም ግንባታ ላይ በተገኙ ውጤቶች እና በቀጣይ በምትሰራቸው ጉዳዮች ላይ ከአጋር አካላት ጋር የምታካሂደውን ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ ጀምራለች። በስብሰባው ላይ ቤተ ክርትያኗ በሠላም ግንባታ ዙሪያ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ደረጃ የነበራትን ሚና በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል። በተለይ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ ምርጫዎችን ተከትሎ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ምሳሌ የሚሆን ተሳትፎ እንደነበራት ተብራርቷል። የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን የሠላም ዋጋ ትልቅ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ''ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሚለምኑ ሰዎች ትምህርት ሊሆኑን'' ይገባል ያሉት ካርዲናል  ብርሃነ ኢየሱስ፤ ''ከጎረቤት አገሮች ጋር በሠላም እየኖርን የውስጥ ሠላም የሚገባውን ያህል አለመሆኑ ሊያሳስበን ይገባል'' ብለዋል። ቤተ ክርስቲያኗ ከጸሎት ጎን ለጎን ሠላም እንዲረጋገጥ የበኩሏን እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰው፤ የቤተ ክርስቲያኗን ሠላም ከማስጠበቅ ጀምሮ ከሌሎች የሐይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባር በትኩረት እያከናወነች እንደሆነ ጠቁመዋል። ''እኛ ኢትዮጵያውያን ዘርና ሐይማኖት ሳንለይ ሁሉንም ማስተናገድ እንደምንችል በታሪክ አስመስክረናል'' ያሉት ካርዲናሉ፤ አሁን አልፎ አልፎ የሚታየው ግጭትና መፈናቀል ከአገሪቱ የመተሳሰብ ባህል የሚበልጥ ባለመሆኑ ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የሚፈታ እንደሆነ አመልክተዋል። ቤተ ክርስቲያኗ በኢትዮጵያ በሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በአገሪቱ እንዲኖር የድርሻዋን ለማበርከት እንደምትተጋ ጠቁመዋል። አገሪቱ በርካታ ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች እንዳሏት ያስታወሱት ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ፤ ቤተ ክርቲያኗ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች እንዲጎለብቱ እንደምትሰራ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው አብዛኛው የግጭት መንስዔ ድህነት መሆኑን በመገንዘብ ቤተ ክርስቲያኗ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል። በትምህርት፣ በጤና በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በግብርናና የአርብቶ አደር ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል። በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከውሃ፣ ከግጦሽ መሬትና ከሌሎች የሀብት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ግጭቶች እንደሚስተዋሉ የጠቁሙት አባ ተሾመ፤ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የሚያግዝ አዲስ ማዕቀፍ በቤተ ክርስቲያኗ መዘጋጀቱን አመልክተዋል። በጀርመን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሚደረገው ድጋፍ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል ያለመ ማዕቀፍ እንዳለ ጠቁመዋል። የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ አርብቶ አደሮች ግብርናን እንዲለማመዱ ማገዝ፣ የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋትና ያለውን ሀብት በጋራ የመጠቀም ልምድ እንዲያካብቱ እንዲሁም ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ ማድረግ በማዕቀፉ የተካተቱ ተግባራት ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም