የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ጨዋታውን ነገ ከዛንዚባር ጋር ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ጨዋታውን ነገ ከዛንዚባር ጋር ያደርጋል
መስከረም 12/2011 የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) ሁለተኛ ጨዋታውን ያደርጋል። በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) አማካኝነት የሚዘጋጀው 6ኛው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ከትናንት በስቲያ በዩጋንዳ መጀመሩ የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም 20 ተጫዋቾችን ጨምሮ 26 ልዑካንን ይዞ ወደ ስፍራው ማምራቱ የሚታወስ ነው። የ11 አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች በሚሳተፉበት ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሁለት ከታንዛንያ፣ ዛንዚባርና ኬንያ ጋር ተደልድሏል። ብሔራዊ ቡድን ትናንት በጂንጃ ከተማ ካኪንዱ ስታዲየም ከታንዛንያ አቻው ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፏል። ለታንዛንያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አልበርት ቺምሳንጋ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሲሰራ ጆን ኬልቪን ቀሪዋን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ የምድቡ ጨዋታውን ነገ በካኪንዱ ስታዲየም ከቀኑ ስምንት ሰአት ከዛንዚባር አቻው ጋር የሚያደርግ ይሆናል። ትናንት በምድብ ሁለት በተደረገ ሌላ ጨዋታ የኬንያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የዛንዚባር አቻውን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ረቷል። ነገ በካኪንዱ ስታዲየም በምድብ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያሸነፉት ኬንያና ታንዛንያ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር በምድብ አንድ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ኤርትራና ጅቡቲ የሚገኙ ሲሆን ሶማሊያ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን በምድብ ሶስት የተደለደሉ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው። በምድብ አንድ ሱዳን በሶስት ነጥብ ስትመራ ዩጋንዳና ኤርትራ በተመሳሳይ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ሲይዙ ጅቡቲ አራተኛ ደረጃን ይዛለች። በምድብ ሁለት ኬንያና ታንዛንያ በተመሳሳይ ሶስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ ኢትዮጵያና ዛንዚባር በግብ እዳቸው ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በምድብ ሶስት ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን በተመሳሳይ አንድ ነጥብ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ እስካሁን በምድቡ ምንም ጨዋታ ያላደረገው የሶማሊያ ብሔራዊ ቡድን ያለ ምንም ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በምድብ አንድና ሶስት ቀጣይ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ። በምድብ አንድ በፔስ ዋር ሞያል ስታዲየም ኤርትራ ከሱዳን ከቀኑ 8 ሰአት አዘጋጅ አገር ዩጋንዳ ከጅቡቲ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን በምድብ ሶስት በካኪንዱ ስታዲየም ከቀኑ 8 ሰአት ደቡብ ሱዳን ከብሩንዲ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። ውድድሩ እስከ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት /ሴካፋ/ የሚያዘጋጀው ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው እ.አ.አ በ1995 በኬንያ አዘጋጅነት ሲሆን ኬንያ ዩጋንዳን በማሸነፍ የውድድሩ የመጀመሪያ አሸናፊ ሆናለች። እ.አ.አ በ2005 በዛንዚባር አስተናጋጅነት በተካሄደው ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያ ብሩንዲን በማሸነፍ አሸናፊ መሆኗ የሚታወስ ነው። ውድድሩ በሴካፋ አማካኝነት በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ሴካፋ ባለበት የፋይናንስ ችግር ምክንያት ውድድሮችን ሳያካሂድ ቀርቷል። ለመጨረሻ ጊዜ የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የተካሄደው እ.አ.አ በ2010 በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ሲሆን ዩጋንዳ ኤርትራን አሸንፋ የዋንጫው ባለቤት መሆን ችላለች። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር /ፊፋ/ ለሴካፋ ውድድሩን እንዲያዘጋጅ ባደረገው የ500 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ውድድሩ ከዘጠኝ ዓመት መቋረጥ በኋላ በድጋሚ መካሄድ ጀምሯል። ዩጋንዳ የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድርን ሁለት ጊዜ ስታሸነፍ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ዛንዚባር እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።