ቀጥታ፡

ለግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ዘመናዊ አሰራር ይፋ ሆነ

መስከረም  12/2012 የሰላም ሚኒስቴር ብሔራዊ የቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር ይፋ አደረገ። ሚኒስቴሩ "ፓክት" ከተሰኘ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ጋር በመሆን ያዘጋጀውን የቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ዘመናዊ አሰራር ይፋ አድርጓል። ፕሮጀክቱ በጋምቤላ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በኦሮሚያ መተግበር ጀምሯል። በተጠቀሱት ክልሎች በ5 ዞን ፣ 12 ወረዳዎችና 60 ቀበሌሎች ላይ ነው የሙከራ ስራውን የጀመረው። አዲሱ አሰራር በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ሲፈጠር ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግስት ፈጥኖ ለማወቅ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። ግጭት ከተነሳበት አካባቢ ከህብረተሰቡ በአጭር የጹህፍ መልክት፣ በመስክ ምልከታና ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን በማሰባሰብ ወደ ተዘጋጀው ዘመናዊ የመረጃ ቋት በማድረስ ጉዳትን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አሰራር ነው። የፓክት የኢትዮጵያ ዳይክተር አቶ አማኑኤል ዲባባ እንደተናገሩት ተግበራዊ በሚደረግባቸው በማሳያነት የተመረጡ ወረዳና ቀበሌዎች ላይ መረጃን ለመሰብሰብ የሚያስችሉ አሰራሮች ተዘርግተዋል። የመረጃውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በሰለጠኑ ባለሙያዎች አማካኝነት ተተንትኖ ምላሽ እንዲያስተባብር  ለተቋቋመው ኮሚቴ ይቀርባል። በአሰራሩ መሰረት በምላሽ አስተባባሪ ኮሚቴው የሚሰጡ ምላሾችንና የሚያስፈልጉ ሰብአዊና ሌሎች እርዳታዎችን በማዘጋጀት ምላሽ ይሰጣል። አሰራሩ በኔትወርክ መቆራረጥና በሃይል እጥረት እንዳይስተጓጎል በወረዳ ኔት አማካኝነት የሚተገበር ሲሆን በሃይል በኩልም አስቀድሞ የተያዘ ሃይል መኖሩን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እያከናወነች ላለው ተግባር ህዝብና መንግስት ተባብረው ግጭትን ለመከላከል መስተጋብር ይፈጥርላቸዋል ተብሏል። የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ እጅጉ በበኩላቸው አሰራሩ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት አጋዥ ነው ብለዋል። ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት መረጃ ከህብረተሰቡ በማግኘት ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት ለመስራትም እንዲሁ። የግጭት አዝማሚያዎች ሲታዩ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ለህዝብና መንግስት መረጃው እንዲደርስ በማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግም የሚያስችል ነው። የሙከራ ትግበራ ከተጀመረባቸው ክልሎች ልምድ በመውሰድ በአገር አቀፍ ደረጃ አሰራሩን በማስፋት ተግባራዊ እንደሚደረግ ሚኒስቴሩ አስታውቀዋል። በአንድ ዓመት የሙከራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት አሰራሩ  ውጤታማ እንዲሆን እንደሚሰራም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል። የአውሮፓ ህብረት፣ የኔዘርላንድ መንግስትና የአሜሪካ የልማት ድርጅት አሰራሩን ለማበልጸግ ድጋፍ አድርገዋል። ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ቀደም ሲል አሰራሩን እየተገበሩት መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም