ቀጥታ፡

በትምህርት ዘመኑ ለሰላማዊ መማር ማስተማር ትኩረት ይሰጣል... የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ

ሀዋሳ (ኢዜአ) መስከረም 12 /2012  በትምህርት ዘመኑ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2012 የትምህርት ዘመን 17 ሺህ  ነባርና ከ5 ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ተመልክቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍስሀ ጌታቸው እንደገለጹት የነባር ተማሪዎች ምዝገባ ከመስከረም 21 እስከ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። ለእዚህም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ በቅድመ ዝግጅትና በአጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት እንደሚወያዩ ተናግረዋል። ዶክተር ፍሰሀ እንዳሉት ከመስከረም 26 ጀምሮ ለነባር ተማሪዎች ትምህርት ይሰጣል። የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ከመስከረም 28 እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ ምዝገባ የሚያካሂዱ ሲሆን ከጥቅምት 3 ጀምሮ ትምህርት እንደሚሰጥ አመልክተዋል ፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች በአዲሱ ሥርአተ ትምህርት እንደሚማሩ ጠቁመው ለእዚህም መጻህፍትና ሞጁሎች መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት። እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው ካሉት ሰባት ካምፓሶች ውስጥ ሦስቱ ተለይተው ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ዝግጁ ሆነዋል፤ ትምህርቱን የሚሰጡ መምህራን ቅጥርም ተፈጽሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ዘንድሮም የዩኒቨርሲቲው መምህራን ክህሎቶቻቸውን የሚያሳድጉበት አጫጭር ሥልጠናዎችን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል ፡፡ የቤተ ሙከራዎችንና የቤተ መጻሕፍትን አቅም ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የ2011 ትምህርት ዘመን በሠላም መጠናቀቁን ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳምቱ ዘንድሮም ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ከአካባቢው ሕብረተሰብና ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም ጉዳይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ለተማሪዎች አገልግሎት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ የተማሪዎች የማደሪያ ሕንጻ፣ የመመገቢያ አዳራሽ እድሳት፣ የሕክምና የመዝናኛ አቅርቦትና ሌሎች አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ይህም በተማሪዎች አገልግሎቶች መጓደል ሊከሰት የሚችለውን የሰላም መደፍረስ ከወዲሁ ለማስቀረት ጠቀሜታው የጎላ ነው” ብለዋል፡፡ እንደ ዶክተር መሳይ ገለጻ ለተማሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚከታተል ግብረ-ኃይል  ተቋቁሞ ወደስራ ተገብቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ከአካባቢው ሕብረተሰብና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሰራቱ በተቋሙ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መስፈኑን ዶክተር መሳይ አስታውሰው ዘንድሮም ይህን ለማጠናከር እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ምግባር ደንቦች ላይ ለተማሪዎች  ሥልጠና እንደሚሰጥ አመልክተው ሕግን የማስከበር ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተማሪ መማክርት፣ ከሠላም ፎረምና ከክበባት ጋር ያለው መልካም ግንኙነት በትምህርት ዘመኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር መሳይ አስረድተዋል ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም