ቀጥታ፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ 13 አዳዲስ የትምህርት መርሃ ግብሮችን ሊከፍት ነው

መስከረም 12/2012 የወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2012 የትምህርት ዘመን በሁለተኛና የመጀመሪያ ዲግሪ 13 አዳዲስ የትምህርት መርሃ ግብሮችን ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ። ተቋሙ በትምሀርት ዘመኑ ከ6 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል። በዩኒቨርሲቲው የድህረ ምርቃ ዳይሬክተር ዶክተር ፍቅሩ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱን ለማጠናከር  አዳዲስ መርሃ ግብሮችን ይከፍታል። በተቋሙ ደረጃ ከሚከፈቱት አዳዲስ የትምህርት መረሃ ግብሮች መካከል 11 በሁለተኛ ዲግሪ ሲሆኑ ይህም በዩኒቨርስቲው የሚሰጠው የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ብዛት ወደ 76 ከፍ ያደርጉታል። እንደ ዶክተር ፍቅሩ ገለጻ አዲስ የሚከፈቱ ፕሮግራሞችን ማስጀመር የሚያስችል የስርዓተ ትምህርት ፣ መማሪያና ማደሪያ ክፍሎች፤ ቤተሙከራ፣ቤተመጻህፍት ፣ ማጣቀሻ መጽሃፍትና የመምህራን ዝግጅቶች ተደርገዋል፡፡ ቱሪዝም ማኔጅመንት፣ ኃይድሮሊክስ ኢንጅነሪንግ፣ በጂኦሎጅና አካካባቢ ለውጥ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጹህፍ ከሚከፈቱት መረሃ ግብሮች ውስጥ ይገኙበታል። በሚከፈቱ የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ350 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምሩ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። "ግቢዉን ማስዋብና ማጽዳት፣ ወንበርና ጠረጴዛዎችን ማደስ፣ ክፍሎችን ማስተካከል፣ መመገቢያ አዳራሾችና ማደሪያ ክፍሎችም ታድሰው ዝግጁ ሆነዋል" ብለዋል፡፡ አዲሱን የትምህርት ፎኖተ ካርታም ለማስተግበር በየደረጀው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች ተደርጓል። ዶክተር ፍቅሩ " ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር ከደሴ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው" ብለዋል፡፡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች የአካባቢውን ህብረተሰብ በወሎ ባህል አርሂቡ ብሎ ለመቀበል ዝግጁ ከመሆኑም ባለፈ የዩንቨርሲቲው አውቶቡሶች ተማሪዎችን ለማጓጓዝ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡ የደሴ ከተማ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ወጣት ይልማ ተረፈ በበኩሉ የወሎ ዩንቨርሲቲ ተማዎሪዎች ሲገቡ በየዓመቱ አቀባበል እንደሚያደርጉ ተናግራል፡፡ ይልማ እንዳለው ዘንድሮም ወጣቶችን በማስተባበር ልዩ አቀባበል ለማድረግ ዝግጁ ናቸው፡፡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ቤተሰባዊ እንክብካቤ እንደሚያድረጉላቸው ገልጿል። "የወሎን ባህል ተምረው አንድነትን ፣ ሰላምና ፍቅር እንዲሰብኩም ከዩንቨርሲቲው ጋር ቀጣይነት ያለው ስራ እንሰራለን" ብለዋል፡፡ ተማሪዎች ደህንነት እንዲሰማቸው ሲመጡ ንብረታቸቸውን በመያዝና በመጠበቅ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው የተናገሩት ደግሞ በደሴ የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት እዮብ መኮነን ነዉ፡፡ "ተማሪዎች የደሴ ከተማ ውበትና ድምቀት ከመሆናቸውም ባለፈ የንግድ እንቅስቃሴውን ስለሚያነቃቁ የንግዱ ማህበረሰብም በልዩ ሁኔታ እንዲቀበሏቸው ድጋፍ እናደርጋለን " ብለዋል፡፡ ወሎ ዩንቨርሲቲ በቀን፤ በማታና በተለያዩ ፕሮግራሞች ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ተመልክቷል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም