ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ አክራሪነትን ለማስፋፋት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተገለጸ

50
መቀሌ ሰኔ 8/2010 ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ አክራሪነትን ለማስፋፋት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ፡፡ 1ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ዛሬ በመቀሌ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡ የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ  ሀጂ መሃመድ ካህሳይ በበዓሉ ስነስርዓት ወቅት እንደተናገሩት የክልሉን ሰላምና ልማት ለማደናቀፍ የሚደረጉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር ይታገላሉ፡፡ በበዓሉ አከባበር ላይ  የተገኙት የመቀሌ ከተማ አስተዳደር  ምክትል ከንቲባ አቶ ብርሃነ ገብረየሱስ በበኩላቸው "ሰላምና የህግ ልእልና የተረጋገጠበት ክልል እንዲሆን ህዝበ ሙስሊሙ የድርሻውን ሚና መጫወት ይገባዋል "ብለዋል፡፡ የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ለሰላምና ለፍቅር ቅድሚያ በመስጠት መሆን እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ የበዓሉ ተካፋይ የሆኑት ሀጂ መሀሙድኑር በሽር ናቸው፡፡ ለዚህም የኃይማኖት መሪዎች አርአያ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ "የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት በመጠቀም ወጣቶች ለሰላም እንጂ ለጥፋት መሰማራት አይገባንም" ያለው ደግሞ ወጣት ጣሂር ዊህብ ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በመቀሌ ስውአት በተባለው ጎዳና በዓሉን ኃይማኖቱ በሚፈቅደው ስነስርዓት ማክበሩን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም