አገራዊ አንድነትንና መከባበርን የሚያዳብሩ በዓላት በስፋት ሊከናወኑ ይገባል-የኢሬቻ ሩጫ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ አንድነትንና መከባበርን የሚያዳብሩ በዓላት በስፋት ሊከናወኑ ይገባል-የኢሬቻ ሩጫ ተሳታፊዎች
መስከረም 11/2012 አገራዊ አንድነትንና መከባበርን የሚያዳብሩና ሕዝባዊ መስተጋብሮችን የሚፈጥሩ በዓላት በስፋት ሊከናወኑ እንደሚገባ ተገለጸ። ሕዝቦች በስፋት ከሚሳተፉባቸው የአደባባይ ሕዝባዊ ባዓላት መካከል አንዱ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለው የኢሬቻ በዓል ነው። በተለይም የሆራ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምት አልፎ የጸደይ ወራት መምጣቱን ተከትሎ በወንዝ ዳርቻ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት የምስጋና ቀን ነው። ኢሬቻ ዘንድሮ ድሮ ከሚከበርበት ቢሾፍቱ 'ሆራ አር ሰዲ' በተጨማሪ በአዲስ አበባ 'ሆራ ፊንፊኔ' እንደሚከበርም ታውቋል። ኢዜአ 'ኢሬቻ ለሰላም' ሩጫ ላይ ያነጋገራቸው አዛውንቶች ኢሬቻ በአዲስ አበባ ዳግም መከበር መጀመሩ የሕዝቦችን አንድነት ያጠናክራል የሚል ዕምነት አላቸው። የ70 ዓመት አዛውንቱ አቶ ተስፋዬ ጀቤሳ እንደሚሉት "አዲስ አበባ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መዲና በመሆኗ ኢሬቻን ለማስተዋወቅ ይረዳል"። ይህ ማለት ደግሞ አንዱ የሌላውን ባህልና ማንነት ሲረዳ መከባበርን መሰረት ያደረገ አንድነት ይገነባል ይላሉ። በመሆኑም በህይወታቸው ኢሬቻ በአዲስ አበባ ሲከበር ለማየት በመቻላቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል። ሌላው የ66 ዓመቱ አዛውንት አቶ አብዱራዛቅ አብደላም እንዲሁ የኦሮሞ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ መልስ አግኝቶ በማየታቸው መደሰታቸውን ይናገራሉ። አቶ አብዱራዛቅ መሰል ሕዝባዊ በዓላት በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል። ሕዝቡ ያለፈበትን የጋራ ታሪክ በማሳብ ለአንድነቱ ሊተጋ ይገባል ያሉት ደግሞ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። ፕሮፌሰር መረራ እንደሚሉት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓላቱን በጋራ በማክበር አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል። ሌላው አዛውንት አቶ ተማም ከበደም እንዲሁ አብሮነትን የሚያጠናክሩ ሕዝባዊ በዓላት በስፋት ማከናወን ጠቃሚ ነው ብለዋል። በተለይም ደግሞ ዘንድሮ ኢሬቻ በአዲስ አበባ መከበሩ ''ለእኔ ዳግም እንደ መወለድ ነው'' በማላት ክስተቱን ገልጸውታል። 'የሆራ ፊንፊኔ' ኢሬቻ በመጪው መስከረም 24 በርካታ ሕዝብ በሚገኘበት ይከበራል ተብሎ ይጠበቃል።