ቀጥታ፡

የጋሞ ዞን የዘመን መለወጫ በዓል መስከረም 13 ይከበራል

መስከረም 11/2012  በጋሞ ዞን የዘመን መለወጫ "ዮ ማስቃላ" ፌስቲቫል መስከረም 13 ቀን 2012 በአርባምንጭ ከተማ እንደሚከበር የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተሻለ ማናዬ እንዳስታወቁት መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ፌስቲቫል በተለያዩ ዝግጅቶች በአርባ ምንጭ ከተማ ይከበራል ፡፡ በጋሞዎች የዘመን አቆጣጠር ቀመር አዲሱ ዓመት በመስቀል በዓል ዕለት የሚጀመር ሲሆን በየዓመቱ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በአብሮነት ሲያከብሩ ለዘመናት ኖረዋል ፡፡ ዛሬም እንደትናንቱ የህዝቡ እሴት የሆኑ ባህላዊ ትዊፊቶች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ለትውልድ ለማስተላለፍ ታልሞ በዓሉ እንደሚከበር አቶ ተሻለ ገልጸዋል፡፡ በበዓሉ ዕለት የጋሞ አባቶች የሰላም ፣ የመቻቻልና የፍቅር ተምሳሌትነታቸውን ጠብቀው በማቆየታቸው በአገር ደረጃ የበጎ ሰዉ ተሸላሚ መሆናቸዉ የሚዘከርበትና ወጣቱ ትዉልድ ይህንን አደራ የሚረከብበት ታሪካዊ ቀን ነዉ፡፡ በተጨማሪም የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር “ከፋን ኢትዮጵያ ስፖርት ተቋም” ጋር በመተባበር 8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ በዞኑ የሚገኙ የጋሞ ፣ የዘይሴና የግዲቾ ብሔረሰቦች ቋንቋ ፣ ባህልና ኪነ-ጥበብ በዓለም መድረክ ከማስተዋወቅም በላይ በቱሪዝም ፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ ትስስር ለመፍጠር ይረዳ ዘንድ በፌስቲቫሉ ላይ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የአከባቢ ተወላጆችን ጨምሮ የክልል የፌደራል ተቋማት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡ ለዚሁ ደግሞ የጋሞ ዞን አስፈላጊዉን ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪው አስታዉቀዋል ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም