ታላቁ የኢሬቻ የጎዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ ተጀምሯል

60
መስከረም  11/2012 የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ታላቁን የኢሬቻ የጎዳና ላይ ሩጫን አስጀምረዋል። "ከብዙ ተጋድሎ በኋላ የደረስንበት የሰላም ሩጫ እንኳን አደረሳችሁ" ሲሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ታላቁ የኢሬቻ የጎዳና ላይ ሩጫን ባስጀመሩበት ጊዜ ነው። መነሻና መድረሻውን መስቀል አዳባባይ ያደረገው ታላቁ የኢሬቻ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ታውቋል። በተጨማሪም 500 የሚደርሱ ተዋቂ አትሌቶች በውድድሩ ላይ ተሳትፈዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው እንደነ ሻለቃ አበበ ቢቂላና ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የመሳሰሉት ጀግኖቻችን ባለፈው በጨለማ ዘመንም ህዝባችን ለአገሩ ምን መስራት አንደሚችል አሳይተውናል ብለዋል። ዛሬም ሰላማዊና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ባህል የሆነውን ኢሬቻን በሩጫ ስንጀምር በአንድነትና በመፋቃቀር የሁላችን የሆነውን ባህላችንን ለማክበርና አገራችን የደረሰችበትን ደረጃ ለማሳየት ነው ብለዋል። የኦዴፓ ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ አርቲስት ዓሊ ቢራ እና አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉና ሌሎም በቦታው ተገኝተው ሩጫውን አስጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም