የመማር ማሰተማሩ ሂደት በፀጥታ ችግር እንዳይደናቀፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል- አምቦ ዩኒቨርሲቲ

61
አምቦ ኢዜአ መስከረም 10 ቀን 2012  በተያዘው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደቱ በፀጥታ ችግር እንዳይደናቀፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረ የጸጥታ ችግር በተያዘው የትምህርት ዘመን እንዳይደገም  ከዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት፣ ከከተማው አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ይሰራል ። በተያዘው ዓመት  ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ከ4 ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎች አቀባበል ለማድረግ የትራንስፖርት አቅርቦትና ሌሎች ዝግጀቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ። በዋናው ጊቢ፣ አዋሮ ፣ ጉደርና ወሊሶ የሚገኙ ካምፓሶች የመማር ማስተማሩን ሥራ በሙሉ አቅም እንዲጀምሩ በዝግጅት ላይ እንዳሉ  ዶክተር ታደሰ አስረድተዋል። በካምፓሶቹ ያልተጠናቀቁ ህንጻዎች የማጠናቀቅና የሚታደሱትን እንዲሁ እየተሰራ  መሆኑን ጠቅሰዋል ። "የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቅጥርም ተካሄዷል" ብለዋል ። በትምህርት ዘመኑ በሁለተኛ ዲግሪ አራትና በሶስተኛ ዲግሪ አንድ አዲስ የትምህርት አይነቶች ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል ። "ተማሪዎች ከፖለቲካ ነፃ ሆነው ሕግና ደንብ አክብረው ትምህርታቸውን በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ በማደረግ ረገድ ከመምህራን ብዙ ይጠበቃል" ያሉት ደግሞ በጉደር ካምፓስ የግብርና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ነጉሴ በቀለ ናቸው፡፡ "ተማሪዎች ጊዜቸውን ለመጡለት ዓላማ ብቻ እንዲያውሉ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡ መምህር ዳዊት ነገሪ በበኩላቸው የ2012 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራን ሰላማዊና የተረጋጋ ለማድረግ ከተማሪ አቀባበል ጀምሮ የተጠናከረ  ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት የተከሰተው የጸጥታ ችግር እንዳይደገም  ፎረም በማዘጋጀት ተማሪዎች እንዲተዋወቁና ባህላቸውን እንዲማማሩ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ። የአምቦ ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ በ106 የትምህርት ዓይነቶች ከ29 ሺህ በላይ አዲስና ነባር ተማሪዎችን  እንደሚያስተምር ዩኒቨርሲቲው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም