ቀጥታ፡

ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ አገር በቀል ባህላዊ የሰላም እሴቶችን ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

መስከረም 10/2012 በኢትዮጵያ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ አገር በቀል ባህላዊ የሰላም እሴቶችን ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ የአፍሪካ ሰላምና ዕርቅ ኢንስቲትዩት ገለፀ። የአፍሪካ ሰላምና ዕርቅ ኢንስቲትዩት ከባለድርሻ አካላት ጋር በዘላቂ ሰላም ዙሪያ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። ተቋሙ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት ሲሆን ከአምስት ዓመት በፊት በአሜሪካ የተቋቋመ እና በአፍሪካ ሰላምና ዕርቅ ማምጣት ዙሪያ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው። ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የትውውቅ መርሃ ግብር ላይ በኢትዮጵያ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ አገር በቀል ባህላዊ የሰላም እሴቶችን ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል። የአፍሪካ ሰላምና ዕርቅ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሸዋፈራሁ ኩራቴ ድርጅቱ የተቋቋመው 'ሰላምና ዕርቅ' የሚሉ ትላልቅ ምሰሶ ሀሳቦችን አንግቦ መሆኑን ገልፀዋል። ልማት፣ የህግ የበላይነት እና ዴሞክራሲ ያለ ሰላም እና እርቅ የማይታሰቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ሸዋፈራሁ፤ ''ሰላም የሁሉ ነገር ቅድሚያ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባል'' ብለዋል። የተቋሙ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ አበራ በበኩላቸው በአህጉሩም ሆነ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶችና ጥፋቶች በሰላም ዙሪያ ያልተሰሩ የቤት ስራዎች በመኖራቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። የተቋሙ የሥራ ትኩረት የሰላም ባህላዊ እሴቶች ተቋማዊ ስብዕና እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ሰላም ከውጪ የሚመጣ ሳይሆን ከራስ የሚፈልቅ መሆኑንን የጠቀሱት አቶ ታረቀኝ፤ አገር በቀል የሰላማዊ እሴቶችን ማጎልበትና ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። የባህላዊ የሰላም እሴቶች የሰላም መቀመሪያ ማዕከላት እንዲሆኑ ተቋማዊ ስብዕናን እንዲላበሱ ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት የጋሞ አባቶች በባህላቸው መሰረት ሊያጋጥም የነበረ ግጭትን ማብረዳቸውን አስታውሰዋል። በሰላም ሚኒስቴር የአገራዊ መግባባት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገዛህኝ ጥላሁን በበኩላቸው ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ለአንድ ወገን የሚሰጥ ባለመሆኑ ሁሉን አካል የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በየአካባቢው ያሉ የዕርቅ ስራ የሚያከናውኑ ባህላዊ የሰላም እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸው፤ መንግስት እሴቶቹን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በውይይቱ ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን በትክክል ስራውን የሚሰራ መንግስት፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈን፣ ሰዎች ግዴታቸውን እንዲወጡና ሙስናን መከላከል እንደሚያስፈልግ ተነስቷል። የንግድ ከባቢ ስነ ምግባር ያለው እንዲሆን እና በቡድኖች መካከል ያሉ የታሪክ ቁርሾዎች በአስታራቂ እውነተኛ ታሪክ እርቅ ሊፈጠር እንደሚገባ ከተወያዮች የተሰጡ ሀሳቦች መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም