የሁለት የውጭ አገር የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ፈቃድ ተሰረዘ

374
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፈቃድ ከሰጣቸው 96 የሁለት የውጭ አገር የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መካከል የሁለቱን ፈቃድ መሰረዙን አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አል-ተያር የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲና አል-ሎዲ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ፈቃድ ተሰርዟል። አል-ተያር የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ስምሪት ባልተጀመረበትና የስምምነት ሂደት ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ሰራተኛ እየመለመለ እንደሚልክ መረጋገጡ ተጠቁሟል። የውጭ አገር ስራ ስምሪት አዋጅ በግልጽ ካስቀመጠው በተቃራኒው በጉዞ ወኪልነት ተግባር ውስጥ ተሳታፊ ሆኖ በመገኘቱና ተደራራቢ የህግ ጥሰት በመፈጸሙ የተነሳ አል-ተያር የተሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ከሚያዚያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ መሰረዙን ገልጿል። በሌላ በኩል አል-ሎዲ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ቀደም ሲል በኤጀንሲነት ሲሰራ ከሶስት ጊዜ በላይ እገዳ እንዳለበት የተደረሰበት በመሆኑ በ2008 ዓ.ም በወጣው የውጭ አገር ስራ ስምሪት አዋጅ መሰረት ከሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ፈቃዱ እንዲሰረዝ መደረጉን ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቁሟል። ህብረተሰቡ የውጭ አገር ስራ ስምሪት ባልተጀመረበትና ከየአገሮቹ ጋር የስምምነት ሂደት ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ በህገ-ወጥ መንገድ ሰራተኛ እየመለመሉ የሚልኩ ህገ-ወጥ ደላሎችና ኤጀንሲዎች ሰለባ ከመሆን እንዲጠነቀቅ ሚኒስቴሩ አሳስቧል። በውጭ አገር ተሰማርተው መስራት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ደህንነታቸው፣ ክብራቸው፣ መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ መስራት እንዲችሉ መንግስት የውጭ አገር ስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ማውጣቱ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም