ቀጥታ፡

በጅቡቲ ወደብ ላይ የጭነት ኮንቴይነሮችን የቆይታ ጊዜ በማሳጠር ከ55 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል

መስከረም 10/2012 በተጠናቀቀው በጀት አመት በጅቡቲ ወደብ ላይ የጭነት ኮንቴይነሮችን የቆይታ ጊዜ በማሳጠር ከ55 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ። የድርጅቱን የ2011 ዓ.ም አፈጻጸምና የ2012 እቅድ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ተሰጥቷል። የድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደገለጹት፤ በጅቡቲ ወደብ ከስምንት ቀናት በላይ  የተቀመጡ ዕቃዎች ተጨማሪ ክፍያ የመፈጸም ግዴታ አለባቸው። ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት አመት በአማካይ የኮንቴነሮች የወደብ ቆይታ ከሰባት ቀናት በታች በማድረግ ይከፈል የነበረውን ተጨማሪ ክፍያ ለማስቀረት መቻሉን ነው የገለጹት። ''ይኸውም የድርጅቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃት ለማሻሻል በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ከተገኙ ውጤቶች አንዱ ነው'' ብለዋል። ወደ ውጭ የሚልኩ ድርጅቶች የክፍያ ቅናሽና የወጪ ማዳን ድጋፍ ማድረግ፣ የዱቤ አገልግሎት የመስጠትና ሌሎች የድጋፍ ስራዎች በበጀት አመቱ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል ናቸው። የድርጅቱን የሎጂስቲክ አገልግሎት አሰጣጥ ዝቅተኛ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ አለመጎልበቱን ገልጸው፤ ''ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት ትግበራ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይጀመራል'' ብለዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች መጓተት፣ በጅቡቲ ድንበር የሚገኝ የመንገድ ብልሽት፣ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ያሉ የቅንጅት ክፍተቶች፣ የቴክኖሎጂ ውስንነትና በደረቅ ወደቦች የእቃዎች ክምችት በበጀት አመቱ ድርጅቱን የፈተኑ ችግሮች መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል። በበጀት አመቱ ከታክስ በፊት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ትርፍ የተገኘ ሲሆን በተያዘው በጀት አመት ይህንን ትርፍ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አቶ ሮባ ተናግረዋል። ''የድርጅቱን ተደራሽነት ማስፋፋት፣ ግንባታቸው የዘገዩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት መተግበር፣ የድርጅቱን ስራዎች የሚመጥን አደረጃጃት ማሟላትና ሌሎች ስራዎች በተያዘው በጀት አመት ከሚከናወኑ እቅዶች ይጠቀሳሉ'' ብለዋል። ቀደም ሲል የማዳበሪያና ስንዴ ምርቶች በውጭ የመርከብ ኩባንያዎች ይጓጓዙ እንደነበር የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ''ከተያዘው በጀት አመት ጀምሮ ስራው ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ እንዲከናወን ተደርጓል'' ብለዋል። ''በዚሁ መሰረት በቂ አቅም ያላቸው ተጨማሪ የውጭ መርከቦች በመከራየት ወደ ስራ ተገብቷል ነው'' ያሉት። እንደ አቶ ሮባ ገለጻ፤ ቀደም ሲል ድርጅቱ ከአንድ ኮንቴይነር ያላነሰ ዕቃ ለሚያጓጉዙ ደንበኞች ብቻአገልግሎት ይሰጥ ነበር ነገር ግን ከ2012 በጀት አመት ጀምሮ የተለያዩ ደንበኞች ዕቃዎች በአንድ ኮንቴይነር ተካተው አገልግሎት የሚሰጥበት አሰራር ተግባራዊ አድርጓል። ይህም በውጭ አገሮች የሚኖሩና የድርጅቱን አገልግሎት የሚፈልጉ ደንበኞችን ጥያቄ የሚያሟላ መሆኑን አቶ ሮባ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች፣ ዘጠኝ ሁለገብ መርከቦችና በየአመቱ ወደ 50 የሚደርሱ መርከቦችን በመከራየት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም