ቀጥታ፡

ለሁሉም ክፍት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 10/2012 ቦሌ በሚገኘው ብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ጅምናዚየም ከመስከረም 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁሉም ክፍት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል። በውድድሩ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ150 በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። በሴት ከ49፣ 57 እና 67 ኪሎ ግራም በታች እንዲሁም በወንድ ከ58፣ 60 እና 80 ኪሎ ግራም በታች ውድድሩ የተካሄደባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። በውድድሩ ማጠናቀቂያ ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል። ከ80 ኪሎ ግራም በታች ወንድ የደቡብ ክልል ተወዳዳሪ ሲያንሰው ዘኪ የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪውን በሪሳ አብዲሳን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን በሪሳ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። የሁለቱ ስፖርተኞች ጨዋታ ተመጣጣኝና ጠንካራ ፉክክር የታየበት ሲሆን የተመልካችን ቀልብ የሳበም ነበር። የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ሲያንሰው ዘኪ ነጥብ ሲያስቆጥርባቸው የነበሩ የተለያዩ ቴክኒኮች ተጋጣሚውን እንዲያሸንፍ አስችሎታል። ቁምላቸው ፈንቴ ከአማራ፣ ስንታየሁ ዘመድኩን ከኦሮሚያ ክልል በዚሁ የክብደት ዘርፍ የነሐስ ሜዳሊ አግኝተዋል። ከ58 ኪሎ ግራም በታች ወንድ የአዲስ አበባው ፍጹም ዘውዱ የደቡብ ክልል ተወዳዳሪውን ባስልኤል ደረጀን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ባስልኤል የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል። ፍጹም ዘውዱ በጨዋታው ከፍተኛ ብልጫ ያሳየ ሲሆን ነጥብ ያስቆጠረባቸው ቴክኒኮችም ብቃቱን አሳይተዋል። አብዱራህማን ሰፋ ከአዲስ አበባ፣ ሁሴን ሀጂ ከኦሮሚያ በዚሁ የክብደት ዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። ከ49 ኪሎ ግራም በታች  የአማራ ክልል ተወዳዳሪዋ ሰብለ ፈለቀ የኦሮሚያዋን ተወዳዳሪ ሶፊያ በለጠን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ሶፊያ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። የሁለቱ ስፖርተኞች ጨዋታ እስከ መጨረሻው ሶስተኛ ዙር የጨዋታ ጊዜ ማብቂያ አሸናፊው ያልተለየበትና ብርቱ ፉክክር የታየበትም ነበር። አፀደ አድማሱ ከኦሮሚያ፣ ማስተዋል ታረቀኝ ከአማራ በዚሁ የክብደት ዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ናቸው። በወርልድ ቴኳንዶ የውድድር ህግ መሰረት በግማሽ ፍጻሜ የተሸነፉ ተወዳዳሪዎች የነሐስ ሜዳሊያ ያገኛሉ። ከ80 ኪሎ ግራም በታች ያሸነፈው ሲያንሰው ዘኪ እና ከ58 ኪሎ ግራም በታች አሸናፊ የሆነው ፍጹም ዘውዱ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተገኙ ሲሆን በስፖርቱ ላይ በታዳጊዎች ላይ መስራት ከተቻለ ጥሩ ውጤት ማምጣት አንደሚቻል ማሳያ የሚሆን ነው። ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡት ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በተጨማሪም አንደኛ ለወጡ የ10 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ ለወጡ የአምስት ሺህ፣ ሶስተኛ ለወጡት ደግሞ የሁለት ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው፣ የፌዴሬሽኑ አቃቤ ነዋይ አቶ አሮን ካሳና በሞሮኮ በተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ከ63 ኪሎ ግራም በታች የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ታሪኩ ግርማ ለተወዳዳሪዎች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል። የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ለኢዜአ እንደገለጹት በውድድሩ የተሻለ ብቃት ያሳዩት ተወዳዳሪዎች እ.አ.አ ለ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሞሮኮ ላይ በጥር 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር የወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ይካተታሉ። የተመረጡት ስፖርተኞች ከመስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅለው ልምምድ መስራት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል። አሰልጣኞች በሚሰጡት ልምምድና ስልጠና ተጣርቶ በወቅታዊ ብቃታቸው የተሻሉት በሞሮኮ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር እንደሚሳተፉም አመልክተዋል። ስፖርተኞች የተወዳደሩባቸው የክብደት ዘርፎች የሞሮኮውን የማጣሪያ ውድድር የክብደት ዘርፎች ታሳቢ ያደረገ ነው። ውድድሩ ለስፖርተኞች የውድድር አማራጭ የፈጠራና ስፖርተኞች ያሉበትን የብቃት ደረጃ እንዲመለከቱ ያደረገም ነበር። በጥር 2012 ዓ.ም በተመሳሳይ ለሁሉም ክፍት የሆነ የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ለማዘጋጀት ፌዴሬሽኑ ዕቅድ መያዙንም አቶ ፍቅሩ አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም