ቀጥታ፡

የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ መከበሩ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ፋይዳ አለው - በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ የከተማው ነዋሪዎች

መስከረም 9/2012 የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ መከበሩ የበዓሉን ባህላዊ እሴቶች በቅርበት ለመመልከት ከማስቻሉ ባሻገር ምጣኔ ኃብታዊ ፋይዳም እንደሚኖረው በመዲናዋ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ነዋሪዎች ለኢዜአ ገለፁ። ለበዓሉ የተለየ ዝግጅት ማድረጋቸውንም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። የምስጋና እና የእርቅ ቀን ተደርጎ የሚወሰደው የኢሬቻ በዓል በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች በየዓመቱ ሁለት ጊዜ ይከበራል። የመጀመሪያው የክረምት መውጣትን ተከትሎ ውሃ በሚገኝባቸው የተፈጥሮ አካባቢዎች፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወቅት በተራራማ ሥፍራዎች ይከበራል። ዘንድሮ ከቢሾፍቱው ሆራ ኤርሰዲ በተጨማሪ በአዲስ አበባም "ሆራ ፊንፊኔ" በዓልን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችለው ዝግጅት ተጠናቋል። የኦሮሚያ ክልል የሚመለከታቸው አካላት ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በዓሉ ባዛሮችን፣ የባህል ፌስቲቫሎችን፣ ሩጫንና የሙዚቃ ኮንሰርትን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል። ኢሬቻ በዓል አካል የሆነው የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ ነገ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፤ በዚህም ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ከመስከረም 12 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት የሚቆይና የኦሮሞ ህዝብን በህል የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቷል፤ ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ህዝባዊ መድረኮችና ትርዒቶችም ይቀርባሉ ተብሏል። በመጨረሻም መስከረም 24 ቀን 2012 ዓም የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በአዲስ አበባ በድምቀት ይከበራል። በዓሉ በአዲስ አበባ በዚህ መልኩ መከበሩ ወደከተማዋ የሚመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳሚዎችን ለማስተናገድ እድል ይፈጥራል፤ ይህም የከተማዋን ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ በማድመቅ በተለይ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች ገበያ እንዲደራ ያደርጋል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል። በአዲስ አበባ ስቴዲየም አካባቢ የታሸገ ውሃንና ደረቅ ምግቦችን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦችን በመቸርቸር የሚተዳደረው ወጣት አሸናፊ አየለ በአካባቢው ህዝባዊ በዓላት ሲኖሩ ሁሌም የተሻለ ጥሩ ገቢ እንደሚያገኝ ጠቅሷል። የዘንድሮው ኢሬቻ በዓልም በአዲስ አበባ መከበሩ እንደርሱ በጎዳና ንግድ ለተሰማሩት የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ ነው ብሏል። በመዲናዋ የሚገኙ ካፌና ሬስቶራትኖንቶችም  ከአሸናፊ ጋር የሚመሳሰል አስተያየት ሰጥተዋለ። በዓሉ ከአዲስ አበባ ውጭ የሆኑ በርካታ ታዳሚያንን የሚያሳትፍ በመሆኑ ለገበያቸው ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉ ገልፀዋል። ይህንን በመገንዘብም ከወትሮው የተለየ ዝግጅት በማድረግ እንግዶችን ለመቀበል መሰናዳታቸውንም ገልፀዋል። የአቡጊዳ ቡናና ካፌ ባለቤት አቶ ጥላሁን አልታዬ በዓሉ አዲስ አበባ መከበሩ የበዓሉን አከባበር በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ተገኝቶ ለመመልከት ያልቻለ በቅርበት እንዲታደመው የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የአገር ውስጥ ቱሪዝምንም ለማሳደግ ያግዛል ሲሉ ገልፀዋል። በዓሉን ለማክበር ወደአዲስ አበባ ለሚመጡ እንግዶች ማድረግ ስላለባቸው ቅድመ ዝግጅት ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር መነጋገራቸውንና የካፌያቸው መለያ የሆነውን ቡና ለማቅረብ እየተሰናዱ መሆኑንም አጫውተውናል። የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ኃይሉ  እንደሚሉት የ"ሆራ ፊንፊኔ" ኢሬቻ በዓል ከረጅም ዓመታት መቋረጥ በኋላ በአዲስ አበባ መከበሩና በመላው አገሪቱም አዲስ የለውጥ ሂደት መጀመሩ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል የተለየ ያደርገዋል። ከዚህም ባሻገር በዓሉ በአዲስ አበባ መከበሩ ሥራ ፈጠራን ጨምሮ የምጣኔ ኃብታዊ ፋይዳው  የጎላ መሆኑን ይናገራሉ። ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ጥሪ አቅርቧል። የኢሬቻ በዓል በተሳካ መልኩ ይፈፀም ዘንድም መላው ህዝብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ተጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም