በአዲስ አበባ የውሃ አገልግሎት ክፍያ ፈጣን ፣ ቀላልና ተደራሽ ሆኗል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የውሃ አገልግሎት ክፍያ ፈጣን ፣ ቀላልና ተደራሽ ሆኗል ተባለ
መስከረም 9/2012 የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች የአገልግሎት ክፍያ ፈጣን፣ ቀልጣፋና በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ባለስልጣኑ የክፍያ ስርዓቱን በማዘመን ለደንበኞቹ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። በባለስልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ስራ እስኪያጅ አቶ ሞገስ ሐብታሙ በሰጡት መግለጫ ቀደም ሲል ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያ ይፈፅሙበት የነበረው በ34 የክፍያ ማእከላት ነው። አሁን ላይ ግን በመዲናዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 350 ቅርንጫፎች ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ መክፈል እንዲችሉ ተመቻችቷል ብለዋል። ደንበኞች በያዙት የእጅ ስልክ በሲቢኢ ብር መተግበሪያ እና በኢንተርኔት ባንኪንግ ክፍያቸውን ባሉበት ሆነው መክፈል የሚችሉ መሆኑንም ገልጸዋል። ደንበኞቹ ርቀት ሳይገድባቸው ባሉበት ሆነው ክፍያ መፈጸም የሚያስችሉ በሞባይል፣ ከባንክ ተቀማጭ በየወሩ ተቀንሶ የሚከፈል እንዲሁም በኢንተርኔት ደንበኞች ተደራሽ የሚያደርጉ አማራጮችን እንዲጠቀሙ በመሆኑም የባለስልጣኑ 566 ሺህ ደንበኞች ክፍያቸውን በተለያዩ አማራጮች በወቅቱ መክፈል ይችላሉ ተብሏል። በአሁኑ ወቅት የክፍያ አማራጩ ምቹ ሆኖ ቢቀርብም ካሉት ደንበኞች መካከል 265 ሺህ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን በንግድ ባንክ አማራጭ ፈፅመዋል። በቀረቡት የክፍያ አማራጮች 30 ሺህ የኮንዶሚኒየም ባለቤቶችና 10 ሺህ ከፍተኛ ውሃ ተጠቃሚ ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎችና ሆቴሎች እስካሁን ክፍያቸውን አልፈጸሙም ተብሏል። በዚህም ባለስልጣኑ 136 ሚሊዮን ብር ደምበኞች የተገለገሉበትን የውሃ ክፍያ እንዳልፈጸሙለት አስታውቋል። የአገልግሎት ክፍያ በማይፈጽሙ ደንበኞች ላይ ከውሃ አገልግሎት ማቋረጥ በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት የሚጠብቃቸው መሆኑንም አቶ ሞገስ ገልጸዋል።