የቱኒዝያ እጩ ፕሬዝዳንት ተወዳዳሪ በእስር እንደሚቆዩ ተገለፀ

73
ኢዜአ፤ መስከረም 8/2012 በቱኒዝያ የምርጫ ሂደት እጩ ተወዳዳሪ ፕሬዝዳንት የሆኑት ናቢል ካሩኢ ከእስር እንዲለቀቁ የተደረገው ጥረት በቱኒዝያ ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉ ታውቋል፡፡ እጩ ተወዳዳሪው ገንዘብን በህገወጥ መንገድ የማዘዋወርና ከታክስ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ በነሃሴ ወር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአልጀዚራ ዘገባ አስታውሷል፡፡ ጠበቃቸው ካሚል ቢን መሱድ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት የይፈቱ ጥያቄ ውድቅ ከሆነ በኋላ “ዳኛው ተገቢውን ውሳኔ ከመስጠት ታቅበዋል፣ይህም ከሃላፊነታቸው ውጪ ነው” ብለዋል፡፡ ከእጩ ፕሬዝደንቱ እስር በፊት ፓርላማው በሰኔ ወር አወዛጋቢ የምርጫ ማሻሻያ ህግ ያፀደቀ ሲሆን በዚህም ካሩኢ በምርጫ እንዳይወዳደሩ የሚያግድ እንደሆነም ዘገባው ያወሳል ፡፡ እጩው እየተሟሟቀ ባለው የምርጫ ውድድር ዝነኛ የሆነው ነስማ የተሰኘው ቴሌቭዥን ባለቤት መሆናቸውና በተደጋጋሚም ለሃገሪቱ ደሆች መድሃኒትና ምግብ ሲመፀውቱ መታየታቸው በተሻሻለው ህግ እንዳይወዳደሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ነው የተገለፀው፡፡ ባለፈው ሀምሌ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ፕሬዝዳንት ቤይጂ ካይድ ኤብሲ ህጉን ሳያፀድቁ ህይወታችው ማለፉም ታውቋል፡፡ የካህሩእ ደጋፊዎች መንግስት በዳኝነት ስርአቱ ተፅእኖ በማሳረፍ እንዳይለቀቁ እያደረገ ነው ቢሉም ክስ አቅራቢዎቹ ደጋግመው ውድቅ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ምንም እንኳን እስር ላይ ቢሆኑም ሊወዳደሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ የገለፀ ሲሆን የሲቪል መብታቸውን የሚነፍግ የተለየ የህግ አንቀፅ እንዳልተቀመጠ መግለፁን ዘገባው አትቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም