ቀጥታ፡

የባህር ዳር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የግንባታ ስራ ተጀመረ

መስከረም 9/2012 በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች ያለሰለስ ድጋፍ በማድረግ ለኢትዮጵያ የእድገት ጉዞ መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት/ጃይካ/ አስታወቀ። ድርጅቱ የባህርዳር ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል 525 ሚሊዮን ብር ወጪ የግንባታ ስራ ማስጀመሩን አስታውቋል። በጃይካ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ተወካይ ሚስ ሃሩካ ናካጋዋ እንደገለጹት የጃፓን መንግስት ኢትዮጵያ የምታካሂደውን ሁሉን አቀፍ ልማት እየደገፈ ይገኛል። ባለፉት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ማሳደግ፣ በትምህርት ተደራሽነት፣ የግል ዘርፉን በማጠናከርና በመስኖና በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ግንባታ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ''በዛሬው እለትም 525  ሚሊዮን ብር በመመደብ የባሀርዳር ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያስችለውን ፕሮጀክት ሙሉ ወጭ መደገፉ የዚህ ማሳያ ነው'' ብለዋል። የውሃ ተቋማት ግንባታው የሚካሄደው በጃፓን ቴክኖ የአማካሪ ኩባንያ/Jpan Techno Co. LTD/ እና ኮኖይኬ /Konoike/ በተባለው የኮንስትራክሽን ድርጅት አማካኝነት በመሆኑ በተያዘለት የጊዜ ገደብና በጥራት አስገንብተው እንደሚያስረክቡ ገልጸዋል። የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ይመር ሃብቴ በቦታ ርክክቡ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የባሀርዳር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ከመቅረፍ ባሻገር የእውቀት ሽግግር የሚካሄድበት ነው። ካሁን በፊትም በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት/ጃይካ/ ካሁን በፊት በክልሉ በሚገኙ ዘጠኝ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በጥራት በመገንባት በተያዘለት ጊዜ ማስረከቡን አውስተዋል። የባህርዳሩን ፕሮጀክትም በተመሳሳይ መልኩ በማከናወን የጃፓን ኩባንያዎች ያላቸውን የስራ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በተሞክሮ ያስተላልፋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ቢሮውም የባህርዳር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ግንባታ በአግባቡ ተከናውኖ ጥቅም ላይ እንዲውል የሃብት፣ የጥራትና የጊዜ ቁጥጥርና ክትትል በየወሩ እንደሚያካሂድ አስረድተዋል። በባህርዳር ከተማ አባይ ማዶ ገብርኤል አካበቢ የሚገነበው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቀን አራት ሚሊየን ሊትር ውሃ የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው የገለፁት ደግሞ የባህርዳር ውሃና ፍሳሽ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ አለሙ ናቸው። በፕሮጀክቱ ግንባታም ስምንት የውሃ ማመንጫ ጉድጓዶች ተቆፍረው የተጠናቀቁ ሲሆን የማጠራቀሚያ፣ የማከሚያና የማቀባበያ የውሃ ጋኖች፣ ስምንት የውሃ ፓንፕ ቤቶች፣ የሰራተኞች መኖሪያና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ቤቶች ግንባታ በኘሮጀክቱ ተካቷል። በተጨማሪም በአባይ ማዶ የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የሚኖረውን ህብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ 52 ኪሎ ሜትር የዋና ዋናና የውስጥ ለውስጥ የቧንባ መስመር ዝርጋታ ይከናወናል ብለዋል። የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አለም ታደሰ በበኩላቸው በጃይካ የሚገነባውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም ለማፋጠን በሳይት ፕላኑ መሰረት 25 በመቶ የሚሆነውን ቦታ ዛሬ ርክክብ ተደርጓል። ቀሪውን ቦታ ለማስረከብ ደግሞ የካሳ ከፈላና የማጽዳት፣ ሶስት የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን በሚገነባባቸው ማዕከላት ለመድረስ የሚያስችል የጠጠር መንገድ ስራና የተቋራጩና የአማከሪ ድርጅቶቹ ሰራተኞች ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ስራ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ሲጠናቀቅ የባህርዳር ከተማ ምስራቃዊ ክፍል የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መቶ በመቶ ከማድረስ ባሻገር አሁን ላይ 60 በመቶ ላይ የሚገኘውን የከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 80 በመቶ ያሳድጋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም